አዲስ አበባ በጽዳቷ ያሳየችው እምርታዊ ለውጥ የሚደነቅ ነው-የጽዱ ከተሞች ኢኒሼቲቭ ተሳታፊዎች

You are currently viewing አዲስ አበባ በጽዳቷ ያሳየችው እምርታዊ ለውጥ የሚደነቅ ነው-የጽዱ ከተሞች ኢኒሼቲቭ ተሳታፊዎች

AMN – የካቲት 14/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ በጽዳቷ ያሳየችው እምርታዊ ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን በጃፓን እየተካሄደ ባለው የጽዱ ከተሞች ኢኒሼቲቭ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

በጃፓን አለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) አዘጋጅነት በጃፓኗ ከተማ ዮካሃማ እየተካሄደ ባለው የጽዱ ከተሞች ኢኒሼቲቭ አዲስ አበባን ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙት በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፣ አዲስ አበባ አሁን በደረሰችበት የዘመናዊነትና የእድገት ደረጃ በቆሻሻ አወጋገድ እና አስተዳደር ላይ ተግባራዊ እያደረገች ያለችውን እቅድና ፖሊሲ መዲናዋን በላቀ ደረጃ ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተቀየሰውን ጠንካራ ስትራቴጂ የሚያመላክት ሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።

ሰነዱን ካቀረቡ በኋላም ከአፍሪካ ከተሞች ሉሳካ፣ ናይሮቢ፣ቱኒዝ፣ አልጀርስ ፣ካርቱም፣ ጁባ፣አቢጃን እና ሌሎችም የመድረኩ ተሳታፊዎች አዲስ አበባ ከተማ በጽዳቱ መስክ ያስመዘገበችው እምርታዊ ለውጥ በእጅጉ የሚደነቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለይም አዲስ አበባ በተቀናጀ የቆሻሻ አስተዳደር ፖሊሲ የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን በሚጠብቅ መልኩ የተቀናጀ መሆኑ፣ ኡደታዊ ምጣኔ ሃብትን ለመተግበር ያለ ጠንካራ ቁርጠኝነት፣ የፕላስቲክ ውጤቶች ጋር ተያይዞ የሚመረቱ የቆሻሻ ምርት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ በጽዳት መስክ ባከናወነችው ጠንካራ ስራ ለተመዘገበው ስኬት በተሰጠው እውቅና የተሰማቸውን ደስታና ኩራት ገልፀዋል።

በሰነዱ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭነት በመቀየር እና በመልሶ መጠቀምና ኡደት ማድረግ ረገድ አዲስ አበባ ልትደረሰበት ያቀደችውን ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ 95 በመቶ ተደራሽነትን በማስፋት ለመሰብሰብ 70 በመቶ ደግሞ ወደ ማስወገጃ ስፍራ ( landfill) የሚሄደውን ቆሻሻ የሚቀንስ ስትራቴጂ በግልጽ በሚያሳይ ፍኖተ ካርታ በማስደገፍ አቅርበዋል።

የጃፓን አለምዓቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ከሌሎች አጋሮች ጋር በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና አስተዳደር ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ እርዳታና መሰል የቴክኒክ ድጋፎች እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

አዲስ አበባ በጽዳቷ በአህጉርና በአለምዓቀፍ ደረጃ እያገኘችው ያለው እውቅና ለጽዱ ከተማና ለዘመናዊ የከተማ አስተዳደር መጎልበት ፈር ቀዳጅ እየሆነች መምጣቷን እንደሚያረጋግጥም መገለጹን ከአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review