አዲስ አበባ ከማይስ ቱሪዝም ያላትን ዕድልና ጸጋ የበለጠ ለመጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing አዲስ አበባ ከማይስ ቱሪዝም ያላትን ዕድልና ጸጋ የበለጠ ለመጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ከኒው ዮርክ እና ጄኔቫ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ እንደመሆኗ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም የበርካታ ሃገራት ኤንባሲዎች መቀመጫ መዲና ናት፡

ከስብሰባ (ማይስ) ቱሪዝም የመጠቀም ዕድሏ ሰፊ በመሆኑ፤ ይህንን ዕድል ለመጠቀም በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያ፣ ተመራማሪ፣ ጸሐፊና መምህር አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ከማይስ ቱሪዝም በሚፈለገው ልክ እንዳትጠቀም ያደረጓትን ምክንያትና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በተመለከተ አያሌው (ዶ/ር) መሠረታዊ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡

በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የሠላም መደፍረሶች፣ በመዲናዋ ያሉት ደረጃቸውን የጠበቁ የኮንፈረንስ ማዕከላት ቁጥር ሁለት ብቻ መሆን፣ የግል ባለሃብቱ በዘርፉ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በዘርፉ የሠለጠነ የሠው ኃይል እጥረት መኖር ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት እና ከዘርፉ የተሻለ ጠቀሜታ ለማግኘት መሠራት ስለሚገባቸው ተግባራት አያሌው(ዶ/ር) እንደጠቀሱት፤ “በሃገሪቱ ሠላም ማስፈን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ስለ አዲስ አበባ ሠላም በመሬት ላይ ያለ እውነታ ተረድተው ከሌሎች የዓለም ሃገራት ወደ ከተማዋ እንዲመጡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የማይስ ቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በከተማ ደረጃ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያነሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የማይስ ቱሪዝም ቡድን መሪ አቶ ለማ ፍቅሬ ናቸው፡፡

ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን የማሻሻል፣ አዳዲስ የመገንባት (የማልማት)፣ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ሆቴሎች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የትራንፖርት አቅራቢዎች፣ አስጎብኚዎች…) ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የመከታተል፣ የመቆጣጠር እና የመደገፍ ተግባራት መከናወናቸው ለዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየት የበኩሉን ድርሻ መጫወቱን አንስተዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ ቢሮው የቱሪስት ሃብትና መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ያለውን የቱሪዝም ሃብትና ጸጋ ለማስተዋወቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ያስረዱት የማይስ ቱሪዝም ቡድን መሪ አቶ ለማ፤ ከተለያየ የዓለም ክፍል ወደ ከተማዋ ለመምጣት ያቀዱ ወይም አቅደው መዲናዋን የረገጡ ጎብኚዎች አስፈላጊ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን ዘመናዊ ስርዓት ለመዘርጋት ቢሮው እየሠራ ነውም ብለዋል ፡፡

በደረጀ ታደሰ

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr

Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9

Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8

Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review