አዳዲሶቹ የቱሪስት መዳረሻዎች

ኢትዮጵያ የፈርጀ- ብዙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ እነዚህ ቅርሶች የኢትዮጵያን ገናና እና ቀደምት የሥልጣኔ ምንጭ ባለቤት መሆኗን አጉልተው የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ሕዝቦቿ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ መሆናቸውን ከሚያመለክቱ እሴቶች ቅርሶች ግንባር ቀደም ሚና አላቸው፡፡ ይሁንና ከእነዚህ መሰል ታሪካዊ ቅርሶች በተጨማሪ በቱሪስቶች ሊጎበኙ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ውብ የመዝናኛ ስፍራዎች እስከ ቅርብ ጊዜ አልነበሩም ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ ግን ለጎብኚዎች ክፍት የሆኑት እንደ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ኮይሻ፣ ወንጪ፣ ጎርጎራ… ያሉ ስፍራዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን የሚደፍኑ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በተለይ መስከረም ወር ብዙ ጎብኚዎች ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት፣ እንዲሁም እንደ መስቀልና ኢሬቻ ባሉ በዓላት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ጭምር ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ የሚንቀሳቀሱበትና ጉብኝት የሚያደርጉበት በመሆኑ አዳዲስ መዳረሻዎች ይበልጥ እንዲጎበኙ፣ አስደሳች የተዝናኖት ጊዜም እንዲያሳልፉ ዕድል ይፈጥራል። ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ጽሁፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሰርተው ለጎብኚዎች ክፍት ከሆኑት ውብ መዳረሻዎችና መዝናኛዎች መካከል ጥቂቶቹን በጨረፍታ እናስቃኛችኋለን፡፡

አዲስ አበባ

ለቱሪዝም አቅም ከሆኑት አዳዲስ መዳረሻዎች መካከል አንዱ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶች ባለቤት እየሆነች ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የውጭ ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆን በሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ጭምር እየተወደዱ ያሉ  ናቸው፡፡ ለአብነትም የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አብርሆት ቤተ- መጻህፍት፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የተለያዩ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ቱሪስቶች በዋናነት ወደ ሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመሸጋገር ገብተው የሚወጡባት ከተማ እንደነበረች የሚታወስ ነው። ይህንን ዝንባሌ የሚቀይሩ ተግባራት  ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በስፋት በመሰራታቸው አዲስ አበባ የምታስጎበኛቸው ተፈጥሯዊ መስህቦችና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ አንጻር ለቱሪዝም ዘርፉም ሆነ ለጎብኚዎች የሚመቹና በሚጎበኙ መስህቦቿ ላይ እሴት ጨምራ መምጣቷ አዲስ አበባ ለመዝናኛው እና ለቱሪዝም ዘርፍ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ እንዲል በር ከፍቷል፡፡

በተለይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት የዓድዋ ድል ጀግኖች በሚገባ ያከበረና የዘከረ  መሆኑ በብዙዎች እንዲወደድ ምክንያት ሆኗል። በቀን ውስጥ በርካታ ሰዎች የሚጎበኙት ይህ ስፍራ፣ ዜጎች የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ታሪክ በቀላሉ እንዲያውቁ በዙሪያው ባሉት ፋውንቴኖችና ውብ ስፍራዎች ፎቶ ግራፍ በመነሳት ትዝታቸውን እንዲያስቀሩ እያደረገ ያለ ነው፡፡ የውጭ ጎብኚዎችም ያለ ጥርጥር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በቀዳሚነት ሊጎበኟቸው ከሚችሉ ስፍራዎች መካከል አንዱ  የዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ጎርጎራ

ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጎርጎራ ፕሮጀክት ውብ ከሚባሉ መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ቱሪስቶችን በቀላሉ የመሳብ ሃይል ያለው የጎርጎራ ፕሮጀክት ገበታ ለአገር የተሰኘው ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ 

በአማራ ክልል በጣና ሐይቅ ላይ የተገነባው ጎርጎራ አንፊ ቴአትር፣ ውብ ሪዞርቶች፣  ሬስቶራንቶችና ሌሎችም የመዝናኛ አገልግሎቶችን በውስጡ ይዟል። ለሰሜን ኢትዮጵያ ሌላኛው ውበት ሆኖ በቅርቡ የተከሰተው ጎርጎራ ሊጎበኙ ከሚገቡ ውብ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ጎርጎራ ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ስፍራ ስትሆን በሰሜን በኩል ከጣና ሐይቅ ጋር ትዋሰናለች፡ ከተማዋ ከጣና ሀይቅ ጋር ገጥማ እንደመገኘቷ ለኑሮ ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ ይዛለች። ጎርጎራ ተፈጥሮ ከለገሰቻት ውብ እይታ በተጨማሪ በርካታ ታሪካዊ ሁነቶችን ያስተናገዱ ቦታዎችን በጉያዋ ይዛለች። አጼ ሱሰንዮስ ዋና ከተማቸውን በ1604 ከጉዛራ ወደ ጎርጎራ እንዳዛወሩ በታሪክ መመዝገቡ በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

አሁን ላይ ከተማዋ ለመዝናኛነት ተመራጭ በመሆኗ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ ለጉብኝትና ለመዝናናት ሲያመሩ ይስተዋላል። ጎርጎራ ሰፊውን የጣና ሐይቅ ክፍል ከነ ግርማ ሞገሱ ማየትና ከከተማ እርቆ ድንቅ ተፈጥሮን በማድነቅ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለቀናት የማይረሳ ጊዜን ማሳለፍ ለሚፈልጉ ትክክለኛ አማራጭ ናት።

ወንጪ

“የምድር ገነት” በሚል ጎብኝዎች የመሰከሩለት ሌላኛው ፕሮጀክት ወንጪ ነው፡፡ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ወንጪ ደንዲ የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተሰርቶ ለጎብኚዎች ክፍት የተደረገ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ የሚገኘው ይኸው ውብ መዳረሻ በስፔን ማድሪድ በተካሄደው በ24ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የወንጪ ሐይቅ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ አይዘነጋም፡፡

ከወሊሶ- አምቦ ጎዳና መሃል ላይ በእሳተ ጎመራ እንደተፈጠረ የሚነገረው የወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ገባውን በድንቅ አረንጓዴያማ ጋራዎች የተከበበ፣ ለዓይን የሚያጓጓ ማራኪ ስፍራ ነው።

ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ደግሞ ከወንጪ ሐይቅ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ መንገድ፣ የአትሌቶች ረዥም ርቀት መሮጫ ትራክ፣ ካፍቴሪያዎችን ጨምሮ፣ ባህላዊ ምግብ ቤቶችና በሐይቁ ዳርቻ የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህና መሰል መዝናኛ ስፍራዎች ደግሞ ጎብኚዎች የአካባቢው ውብ መልክዐ-ምድርና ተፈጥሮን ከመጎብኘት በተጨማሪ ዘና ፈታ እንዲሉ ምቹ ጊዜን ፈጥሯል፡፡

የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት አካል የሆነው የወንጪ ሐይቅ ከ170 የቱሪዝም መንደሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ መመረጡ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ወደ ሃገራችን እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አል አይን የተባለ መገናኛ ብዙሃን በገጸ- ድሩ አስነብቧል፡፡

ኮይሻ

በገበታ ለሀገር ተገንብተው ለጎብኚዎች ክፍት ከሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብ ምዕራብ ክልል፣ በኮንታ ዞን የሚገኘው ኮይሻ አንዱ ነው፡፡ አካባቢው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ ሲሆን፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦችም መኖሪያ ነው።

የኮይሻ ፕሮጀክት የአካባቢውን ታሪክ እና ባህል እንዲሁም የተፈጥሮን እና የሰው ሰራሽ ሀብቶችን አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ረዥም እድሜ ያስቆጠረውና ሃላላ ኬላ የተባለው የድንጋይ ካብ እዚሁ ውስጥ ይገኛል። በዳውሮ ሕዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የተገነባው የድንጋይ ካብ ወይንም ኬላ በግምት ብዙ ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው። በአካባቢው ማህበረሰብ ‘ካቲ ሃላላ ኬላ’ ይሉታል። እነዚህን ታሪካዊና በቅርቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ያከለው ይህ ስፍራ ኢትዮጵያ አሁን ላይ አሉኝ ከምትላቸው ምርጥ የመዝናኛ መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ኮይሻ በውብ ተፈጥሮና መልክዐ ምድር የታጀበ ድንቅ ስፍራ ሲሆን፤ ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ትውፊቱን እንደጠበቀ የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ላይ በሃገራችን ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review