ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አበይት አጀንዳዎች መካከል “አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን መፍጠር” የሚለው አንዱ ነው፡፡ ህብረቱ አፍሪካ ይህንን ምኞቷን እንድታሳካ ፖሊሲ አውጥቶ እየሰራ ሲሆን ግጭትን ለመከላከልና ለመፍታት ደግሞ በውይይት ላይ ያተኮረ አቀራረብን ይከተላል፡፡
እንደ አፍሪካ ህብረት መረጃ ከሆነ በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን ቁልፍ የሆነው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለመፍታት ቋሚ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው።
ህብረቱ፤ ምክር ቤቱን በአፍሪካ ውስጥ ለሚከሰቱ ግጭቶች እና ቀውሶች ወቅታዊ እና ቀልጣፋ ምላሾችን ለማመቻቸት ይረዳው ዘንድ አስቦ የመሰረተው ስለመሆኑም የአፍሪካ ህብረት በይፋዊ ገፀ ድሩ ባሰፈረው መረጃ ተመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሰላም እና ደህንነት መምሪያ (PSC) ፕሮቶኮል የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ይደግፋል፤ እንዲሁም በአህጉሪቱ ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ይመራል።
ዲፓርትመንቱ የአፍሪካን የሽብር ጥናትና ምርምር ማዕከል በበላይነት ይቆጣጠራል። ይሁን እንጂ ይላል የህብረቱ መረጃ በትጥቅ የታገዙ የጎሳ ግጭቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ብጥብጥ መሰል ነውጦች በአህጉሪቱ ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት ላይ ትልቅ ፈተና ሆነዋል። በመረጃው መሰረትም እ.ኤ.አ. በ1960 እና 1990 መካከል በአፍሪካ 18 የእርስ በርስ ጦርነቶች ተከስተዋል፡፡ በዚህም ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ሲሞቱ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተሰደዋል፡፡

አፍሪካ ለዚህ ችግር የተዳረገችው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ያልተረጋጉ ወይም ደካማ ተቋማት መኖር፣ ደካማ የፖለቲካ ስርዓት እና ከአፍሪካ ችግሮች ጋር ያልተጣጣሙ ፖሊሲዎች እንደሆኑም የናይጄሪያው ኦዮ- ኢኪቲ ዩኒቨርሲቲ በአረቢያን ጆርናል ኦፍ ቢዝነስ እና አስተዳደር ላይ “የአፍሪካ ህብረት እና የግጭት አፈታት” በሚል ርዕስ ያሳተመው ጥናታዊ ፅሑፍ ያመለክታል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ ለዚህም እንብዛም የተስፋፋ ባይሆንም ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሳሙኤል ሺበሺ እንደሚሉት አፍሪካ የራሷን ሰላም በራሷ የማስጠበቅ ትልቅ ዕድልና አቅም ቢኖራትም የህብረቱ አባል ሀገራት በሙሉ ልብና ዕምነት መስራት ባለመቻላቸው፣ በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ በምክክር ለመፍታት ጠንክረው ባለመስራታቸውና በመካከላቸውም መተማመን በሚገባው ልክ ባለመስፈኑ አፍሪካ ሰላሟን በራሷ ማስጠበቅ አልቻለችም፡፡
እንደ አፍሪካ ህብረት (AU) መረጃ ደግሞ ለአፍሪካ የሰላም እጦት የግዛት ውዝግቦች፣ የታጠቁ ጎሳዎች በየጊዜው የሚያነሷቸው ግጭቶች አለፍ ሲልም የእርስ በርስ ጦርነቶች እና በአንዳንድ ሀገራት የመንግስት ስልጣንን በሀይል ለመናድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህም ከአህጉሪቱ አልፈው ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ዋና ስጋቶች እንደሆኑም ተገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት በይፋዊ ገፀ ድሩ የግጭት አፈታት፣ ሰላምና ደህንነት (Conflict Resolution, Peace & Security) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የአፍሪካን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆነው የመጀመሪያው ችግር የበጀት እጥረት ነው። ይህም የገንዘብ እጥረት በዘመነው ዓለም ላይ ውስብስብ የደህንነት አስተዳደር ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነበት ጠቁሟል፡፡
የገንዘብ እጥረት በመኖሩ በሁሉም የአህጉሪቱ ክፍል አስተማማኝ የፀጥታ ሀይል ለማስቀመጥና ችግሮችን ከመፈጠራቸው በፊት ለማስቀረት ሲፈጠሩም በአፋጣኝ ለመቆጣጠር እንዳልቻለ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ይላል የህብረቱ መረጃ አፍሪካውያን ለሰላም ፈንድ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በማዋጣት ሊሰሩ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ህብረቱ የሰላም ተልዕኮውን ያለምንም ጣልቃ ገብነት ለማከናወን ይረዳዋል ሲልም ያሳስባል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሰላምንና ደህንነትን በማረጋገጥ የማይናቅ ሚና መጫወቱን የሚገልፁት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ሙሀመድ በሽር በበኩላቸው አፍሪካ ካለባት የውጭና ውስጥ ውስብስብ ችግር አንፃር ከነችግሩም ቢሆን ህብረቱ በሰራቸው ስራዎች አንፃራዊም ቢሆን በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ሰላምን ማስጠበቅ ተችሏል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ይፋዊ ገፀ ድር በሰፈረው መረጃ እንደተመላከተውም አልሸባብን ከሞቃድሾና ከኪስማዩ በማስወጣት በሶማሊያ በህዝብ ተቀባይነት ያለው መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመስርቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል አስተዋፆ እና የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ ስፍራ እንዳለው አይዘነጋም፡፡ በዳርፉርም የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሌሎች የተሻለ አፈጻጸም አለው፡፡ በዝምባቢዌ ድህረ ምርጫ የተከሰተውን ብጥብጥ የአፍሪካ ህብረት ዘግይቶም ቢሆን በብቃት መፍታት እንደቻለም የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሳሙኤል እንደሚሉት የአፍሪካ ህብረት ከሌሎች ዓለማችን ህብረቶች ትምህርት መውሰድና እራሱን የሚመስል አደረጃጀትም ሆነ ቁመና ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ይላሉ ምሁሩ የአውሮፓ ህብረት የተረጋጋና በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት አባላት ያሉበት ሲሆን አደረጃጀቱም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ አባላቱ ለአውሮፓ ሰላምና ብልፅግና በሙሉ እምነት የሚጠበቅባቸውን ያደርጋሉ፡፡ በአፍሪካ ግን አሁንም የእርስ በርስ ግጭት የሚታይባቸው ሀገሮች አሉ፡፡ ስለሆነም ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አደረጃጀትና አሰራር ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡
ከሌሎች አህጉራት ባሻገርም ህብረቱ በአህጉሪቱ ካሉ አደረጃጀቶችም ትምህርት መውሰድ አለበት፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ያሉ ውጤታማ አካባቢያዊ አደረጃጃቶችን ለምሳሌ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ECOWAS/ እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /IGAD/ ከመሳሰሉት ልምድ መውሰድ መቻል አለበት፡፡ የህብረቱ በጀት በሌሎች አካል መሸፈን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው አባል ሀገራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በወቅቱ በመክፈል የህብረቱን የማስፈፀም አቅም ማሳደግም እንዳለባቸውም ሳሙኤል ሺበሺ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከስኬቱም ሆነ ከልምዱ ለመማር የሚያስችለው ከግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ የእድሜ ባለፀጋ ነው። በመሆኑም የወደፊት አቅጣጫውን ሲተልም ያለፈውን ጉዞ በሚገባ መመልከት አለበት፡፡ የቆመበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቆ መረዳትና መጭውን በሚገባ መመልከትና በዚያው ልክ መዘጋጀትም ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት፣ ተሳትፎን ማሳደግ፣ የገቢ አቅምን ማሳደግ፣ መሪዎች እርስ በእርስ ተናበውና ተግባብተው መስራትና ለአፍሪካ ሰላም ሁሉም ዘብ መቆም እንዳለባቸው ሳሙኤል ሺበሺ ገልፀዋል፡፡
የእንግሊዙ በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ “የአፍሪካ ሰላም እና ማህበራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚረዱ መንገዶች” በሚል ርዕስ በ2024 ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት በአፍሪካ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ህዝብን ያሳተፈ ውይይት፣ ተጎጂዎችንም ሆነ አጥፊዎችን ሳያርቁ በዳይ በደሉን አምኖ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ፣ ተበዳይን መካስና ከልብ ይቅር እንዲባባሉ ማድረግ ያስፈልጋል ይላል ፡፡
እንደ መረጃው ከሆነ በአፍሪካ ያሉ ዕድሜ ጠገብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ለአፍሪካ ሰላም በጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ ጥቅም ላይ ቢውሉ የአፍሪካን ሰላም በአስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባት ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በየሀገራቱ ድንቅ ባህላዊ እሴቶች አሉ ይላል ጥናቱ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ሙሀመድ በሽር እንደሚሉት የአፍሪካ ሰላምና እድገት ዘለቄታዊ ለውጥ እንዲያመጣ አፍሪካዊ ወዝ ያላቸው ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ እስካሁን ባለው እውነት አህጉሪቷ እነዚህ ተቋማት በሚፈለገው ልክ የሏትም፡፡ በዚህም የአፍሪካ ህብረትም አልሞና አንግቦ የተነሳውን ዓላማ ማሳካት አልቻለም፡፡
አፍሪካ ሰላሟ የተጠበቀና እድገቷም የቀጠለ እንዲሆን የቀጣናዊ ትስስሩ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ መሰረቱም በአባል ሀገራቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊፀና ይገባዋል፡፡ ለአፍሪካዊያን ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ እንዲፈታ ጠንክሮ መሰራት አለበት፡፡ አፍሪካውያን እምነታቸው በህብረቱ ላይ እንዲሆንም መጣር ይኖርበታል፡፡
ስለ አፍሪካ ሰላም በሰፊው ውይይት የተደረገው እ.ኤ.አ. በግንቦት 25 ቀን 2013 የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና አጀንዳ 2063 በተጀመረበት ወቅት ነው። ከዋና ፕሮጄክቶቹ አንዱ የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን ማየት ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ዓላማው በታሰበው ልክ ሊሳካ እንዳልቻለ የህብረቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት፣ ከችግሩ ስፋት አንፃር ህብረቱ በቂ በጀት አለመኖር፣ በአህጉሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ውስብስብ መሆናቸው እና የሰላም ስምምነቶችን የማስከበር አቅም ማነስ ለህብረቱ ዓላማ አለመሳካት እንደምክንያት ተነስተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ፍላጎትና አመራርን ማጠናከር፣ የፋይናንሺያል ድጋፍን ማሳደግ፣ የግጭት መንስኤዎችን መፍታት፣ የሰላም ማስከበር እና የሽምግልና አቅሞችን ማሻሻል፣ የአፍሪካ ተጠባባቂ ሃይልን ማጠናከር እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሙን ማሻሻል ቀጣይ ቀውሶችን ለመቋቋም ወሳኝ እንደሚሆኑም ተጠቅሰዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ