AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
አፍሪካ በዓለም አቀፋዊ መድረኮችና በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እንድትሆን አህጉራዊ ስትራቴጂካዊ ውይይትና የጋራ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ለዚህም የአህጉሪቱ መሪዎች የፖሊሲ መናበብን በመፍጠርና በጋራ ጉዳዮች በመስማማት አህጉራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የማረጋገጥ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “አሁናዊ የዓለም ሥርዓትና በአፍሪካ ላይ ያለው ተፅዕኖ” በሚል ርዕስ የመወያያ ሀሳብ አቅርበዋል።
አፍሪካ ከዓለም ቀዳሚ የሥልጣኔ መሠረቶች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ግን ወደ ኋላ ከቀሩ የዓለም ክፍሎች መሆኗ ሊያስቆጭ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የአፍሪካን ትንሳኤ እውን በማድረግ በዓለም መድረክ ተገቢውን ቦታ እንዲኖራትና ተፅዕኖ እንድትፈጥር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸውና በዓለም ሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትርጉም ያለው መፍትሔ ተኮር ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የአህጉሪቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ አብነታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ አፍሪካ በዓለም ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እንድትሆን ስትራቴጂካዊ ውይይቶችና ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
አሁን ላይ አህጉሪቱ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ግልፅና የተናበበ የመፍትሔ ማዕቀፍ አለመኖሩንም ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የዓለም ሥርዓቶች ለአፍሪካ የማይመቹና ጉዳቶችን ያስከተሉ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በድኅረ የዓለም ጦርነት በነበረው ሥርዓት ውስጥ የአፍሪካ እሳቤዎች ወደ ጎን ተብለው እንደነበር አውስተዋል።
ለረዥም ጊዜያት አፍሪካ የውጭ እርዳታና ብድር ጥገኛ ሆና መቀጠሏን በመጥቀስ፤ ጥሬ የተፈጥሮ ኃብቷም ሲመዘበር መቆየቱን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባለፈ አፍሪካን የጦርነት ቀጣና በማድረግ ለብዙ ጉዳት እንደዳረጋት አንስተዋል።
በዚህም ራስን ለመቻል ያለመ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ማንበር ላይም ውድቀቶች እንደነበሩ አውስተዋል።
የሉላዊነት መስፋፋትን ተከትሎ በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ አዳዲስ ኃይላት መምጣታቸውን ገልጸው፤ ቻይና ህንድና ሌሎችም የእስያ ሀገራት ሉላዊነትን ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ሲጠቀሙበት በአንጻሩ አፍሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን ተናግረዋል።
አሁንም መሠረታዊ የዕይታና የስትራቴጂ ለውጥ ካላደረግን አፍሪካ በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥም ተጎጂ ሆና የመቀጠል ስጋት እንደተደቀነባት ጠቁመዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት አንድነታቸውን በማጠናከር አህጉራዊ ፍላጎትና ጥቅምን ለማሳካት በአንድ እሳቤ፣ በአንድ ድምፅ፣ በተባበረ ኃይል መሥራት አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም ስትራቴጂካዊ ውይይቶችን በማድረግ ወጥ ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ በዓለም መድረክ በሚኖር ተገቢ ውክልና ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝና ተፅዕኖ ፈጣሪ አህጉርን መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአፍሪካን መፃዒ ሁኔታ በአዲስ መልክ ለመቅረፅና በዓለም አቀፋዊ መድረክ ጉልህ ሚና ለመጫወት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡