አፍሪካ የምትሻው የዓድዋ መንፈስ

You are currently viewing አፍሪካ የምትሻው የዓድዋ መንፈስ

ለ128ኛ ጊዜ በተከበረው የዓድዋ ድል ክብረ በዓል ሲምፖዚየም ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤሜሬተስ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ የዓድዋ ድል ትሩፋቶች ምንድን ናቸው? በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን በጥሷል፤ ኢትዮጵያንም የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏል ብለዋል። ድሉም በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች ዘንድ የፓን-አፍሪካዊነት እንቅስቃሴ እንዲያብብና የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ቅኝ ግዛት ነው፤ የነጮች ደግሞ የገዥነት የሚለውን እሳቤ ስለመሻሩም ይጠቅሳሉ።

በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ2011 ጃናስ ሬመንድ “The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸውም፣ የገዢና የተገዢነት ኋላ ቀር እሳቤን ከመሻሩም በላይ አፍሪካውያን በተባበረ ክንድ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማስወገድ እንዲችሉ የዓድዋ ድል አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ለዚህም ነው የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞተሊ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ነፃነት ትግል እንደ ችቦ መቀጣጠያ ሆኖ ማገልገሉን ጠቅሰው አፍሪካ በዓድዋ ድል መንፈስ ልትታደስ ይጋባል ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አፍሪካ የታገረጡባትን ፈተናዎች መሻገር የምትችለው በዓድዋ ድል መንፈስ ስትታደስ ነው ይበሉ እንጂ አፍሪካውያን በተባበረ ክንድ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማስወገድ ቢችሉም የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማስቀረት አልቻሉም። እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ታዲያ አህጉሪቱ ከነጻነት በኋላ ከእጅ አዙር ተፅዕኖ ለምን መላቀቅ ተሳናት? በቀጣይስ በዓድዋ ድል የተለኮሰው የነጻነት ችቦ እየጎለበተ እንዲሄድ የአህጉሪቱ የቤት ስራ ምንድነው የሚለው ነው?፡፡

አህጉረ አፍሪካ ቦታና ወቅት እየቀያየረ የሚመጣ ግጭትና አለመረጋጋት፣ አሳሳቢ ድህነት፣ የውጭ ሀገራት ያልተቋረጠ ጣልቃ ገብነት ጋር ተደማምሮ የዓድዋ ድልን ፍሬ በቅጡ ሳታጣጥም ቀጥላለች። ካሜሩን የሚገኘው ያውንዴ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጌራርድ-ማሪ ሜሲና በአፍሪካ ጉዳዮች በሚተነትነው አፍሪካና ጆርናል ጦማር ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት በእጅ አዙር አህጉሪቷን የሚዘውሯት አንዳንድ ሀገራት ከአህጉሪቱ በሚወሰዱ ጥሬ እቃዎች እሴትን በመጨመር ራሳቸውን ማበልጸግ የቻሉ ሲሆን፣ አፍሪካ ግን አሁንም በግጭት አዙሪቱ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል፡፡

‘ማን ያውጋ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ’ እንዲሉ ፓን አፍሪካኒስቱ ኩዋሜ ኑኩሩማ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ  ስርዓትን አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር ለጉዳዩ ጠቅለል ያለ ምስል የሚሰጥ በመሆኑ እዚህ ጋር መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ “የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ፍሬ ነገሩ በሥሩ ያለን ሀገር የይስሙላ ነፃነት እንደ አንድ ብሔራዊ ህልውናውን እንዳስከበረ ሀገር አስመስሎ ማቅረቡ ሲሆን፣ በተጨባጭ ግን እውነታው የሚያረጋግጠው የሀገሩ የኢኮኖሚ አወቃቀርና አሠራር የፖለቲካ ፖሊሲ የሚመራው ከውጭ መሆኑን ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡

ይህም ማለት አሁንም በአፍሪካ የእጅ አዙር ተፅዕኖ መቀጠሉንና አሁንም ቢሆን አፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የባህል እና የፖለቲካ ነፃነት አላት ማለት እንደማይቻል ነው፡፡ ለዚህም ጥቂት ማስረጃዎችን ወደማንሳቱ ከማለፋችን አስቀድመን አፍሪካ ላይ ለምን የሙጥኝ አሉ ለሚለው ጉዳይ ማሳያ ይሆን ዘንድ ከባህር ላይ የጭልፋ ያህል የተባበሩት መንግስታት አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራምን ዋቢ አድርገን አንዳንድ የአህጉሪቱን እውነታዎች እንጥቀስ። አስራ ሰባት በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ብዛት መያዟ፣ 90 በመቶ የሚሆነው የዓለም ፕላቲኒየም የሚገኝባት አህጉር መሆኗ እንደዚሁም ከዓለም ወርቅ አቅርቦት ግማሹ እና 35 በመቶ ዩራኒየም በውስጧ መገኘቱ በተጨማሪም 90 በመቶ የሚሆነው አንጸባራቂ ብረት የሚገኘው በአፍሪካ መሆኑ አህጉሪቱ ላይ እንደሙጫ እንዲጣበቁባት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

የሆነው ሆኖ አፍሪካ አሁንም ድረስ የእጅ አዙር ተፅዕኖ ነጻ አለመሆኗና የኢኮኖሚ፣ የባህል እና የፖለቲካ ነፃነት አላት ማለት እንደማይቻል በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አህጉሪቱ ከዓይናቸው እንድትርቅ የማይፈልጉት ምዕራባውያኑም አንዳንድ ጊዜ የጦር ሰፈር በመገንባት፣ በሌላ ጊዜም በዲፕሎማሲ እና በንግድ ስም መለስ ቀለስ እያሉ አፍሪካን ሲበዘብዟት ኖረዋል፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳን ”የኃያላን“ ሀገራት ዓለምን ከጫፍ አስከ ጫፍ ለመቆጣጠር ያላቸው ፍላጎት ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ፣ እጃቸው እየረዘመ መምጣቱና ከፍላጎታቸው በተቃራኒ የቆመን የትኛውንም መንግስት ለመቆጣጠር የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለም የናይጄሪያ ንናምዲ አዚኪዌ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ተንታኙ አንዲ ቹኩዋሜካ ይገልጻሉ፡፡

አሁን ላይ ደግሞ ዓለም በደረሰችበት ፖለቲካ አውድ በሀገራት ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ከሚደረገው ተጽዕኖ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፣ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች እና የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ዋነኞቹ የፖለቲካው ጣልቃገብነት መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ አፍሪካውያን ዜጎች ልክ እንደ ቁስ ገበያ ላይ በሚቸረቸሩበት ወቅት በአድዋ ድል ብርሃን ፈንጣቂነት ማብቂያ ያግኝ እንጂ አህጉሪቱ አሁንም ቢሆን ነጻነቷን ሙሉ በሙሉ ለማወጅ ቀሪው መንገድ ገና ብዙ ነው፡፡ እዚህ ጋር የሚነሳው ሌላኛው ጥያቄ ግን አፍሪካውያን ይህ እንዳይሆንባቸው ምን ሰሩ በቀጣይስ በአፍሪካ እጣፈንታ ላይ በዋናነት ወሳኟ ራሷ አፍሪከ እንድትሆን ምን ይጠበቃል የሚለው ነው፡፡

አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ለመኖር ጊዜው ያለፈበት ቢሆንም ዛሬም ድረስ ዓይኑን አፍጥጦ የሚታየውን እውነት ለመቀየር ዞር ዞር ሸክሙ ቅድሚያ የሚያርፈው በአፍሪካውን መንግስታት ትከሻ ላይ ስለመሆኑ ንናምዲ አዚኪዌ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ተንታኙ አንዲ ቹኩዋሜካ ያስረዳሉ፡፡ አፍሪካውያን የቅድሚያ ቅድሚያ የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አንዲ ቹኩዋሜካ  ሲቀጥልም በዓለም ላይ አግላይና ኢፍትሃዊ አሰራሮችን ለማስወገድ፤ አፍሪካውያን በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ዓለም በርካታ ዜጎቿ ለተሸከሙት መከራ ሰብዓዊ እርዳታ ለድርድር ባይቀርብም ሁሉም ለእርዳታ የሚዘረጉት ክንዶች ግን ለጽድቅ ብቻ የተዘረጉ አለመሆናቸውን መገንዘብም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ይህ የፕሮፌሰሩ አስተያየት ደግሞ ከባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ሀሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል። ወይዘሮዋ ”አፍሪካ ከለጋሾች ስንዴ ይልቅ በለም መሬቷ እና በልጆቿ እጆች መተማመንን ስትመርጥ በዓድዋ መንፈስ ትታደሳለች። ስንዴ የሚለምኑ የአፍሪካ እጆች የታላላቆቻቸውን ዳና ተከትለው እምቢኝ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በማለት ትራክተር መጨበጥ አለባቸው“ ነበር ያሉት፡፡ እዚህ ጋር ታዲያ በዓድዋ መንፈስ በመታደስ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው ስኬት ተጨባጭ ተሞክሮ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደተመላከተው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላለች፡፡

በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶ/ር አዴኦዬ ኦ አኪኖላ አስተያየት ደግሞ  በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታን እውን ለማድረግና የፖለቲካ ነጻነትን ለመቀዳጀት ቁልፉ ያለው መሪዎቿ ጋር ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ለችግሮቻቸው አህጉራዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ከሊበራሊስቶች የበለጠ ሊበራል ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ከምዕራባውያን የበለጠ ምዕራባዊ ለመሆን ስለሚቃጣቸው ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለጉን ይዘነጉታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ስለሆነም ከዚህ አካሄድ ወጥተው   ”ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካውያን መፍትሄዎች“ መርህ ላይ መቆም ይኖርባቸዋል ሲሉም ይመክራሉ።

የጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪውና “Digital colonialism: US empire and the new imperialism in the Global South” መጽሐሰፍ ደራሲው ሚካኤል ክዌት ደግሞ ጉዳዩ ከዚህም ይሻገራል ባይናቸው፡፡ተመራማሪው እንደሚሉት በቀድሞዉ እሳቤ  “ቅኝ ገዥነት”  በሌሎች  ሀገራት ዉስጥ ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችንና  ተቋማትን  የመቆጣጠርና  በባለቤትነት የመያዝ  ተግባር  ሆኖ  እናገኘዋለን።  ይህ  ዓይነቱ  የብዝበዛ  ሂደት  ለብዙ  መቶ  ዘመናት  በዝግመተ  ለውጥ  የተገኘ  ሲሆን  አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች  መፈጠር  ደግሞ  ጉዳዩን ወደ  ድብልቅ ቅኝ ግዛት እሳቤዎች እንዲገባ አድርጎታል ይላሉ።

የሆነው ሆኖ የአህጉሪቱን ለዓመታት ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጊዜ የሚጠይቅ ስለመሆኑ አያካራክርም፡፡ መፍትሄው ግን በዋናነት የሚገኘው ከራሳቸው ከአፍሪካውያን እንደሆነ አምነው መሪዎቿ ወደ ውጪ ማማተሩን መተውና ሌላው ዓለምም ወደ አፍሪካ የሚሰነዝረውን እጅ እንዲሰበስብ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ እንዳሉት አፍሪካ የታገረጡባትን ፈተናዎች መሻገር የምትችለው በዓድዋ መንፈስ ስትታደስ ነው፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review