AMN – መስከረም 23/2017 ዓ.ም
የኢሬቻ በዓል የመከባበር እሴት እና የትውልድ ቅብብሎሽ የሚታይበት መሆኑን ሀዳሲንቄዎች ተናገሩ።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜ መስከረም 25 በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ መስከረም 26 እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በድምቀት ይከበራል።
ይህንም አስመልክቶ ሀዳሲንቄ ዘውዲቱ ጌታቸው እንዳሉት የኢሬቻ በዓል የመከባበር እሴት እና የትውልድ ቅብብሎሽ የሚታይበት ነው።
በዓሉ በሚከበርበት ቦታ በሚከናወነው ስርአት በቅድሚያ ልጃገረዶች ከፊት የሚመሩ ሲሆን በመቀጠል ሀዳሲንቄዎች እንዲሁም ሴት አዛውንቶች ተከታትለው እንደሚጓዙ ጠቅሰዋል፡፡
ከእነሱ ቀጥሎ አባገዳዎች በረድፍ እንደሚሄዱና ከእነሱ ቀጥሉ ፎሌዎች ከዛም ሌሎች ይከተላሉ ብለዋል።
በኢሬቻ እሴት መሰረት ሂደቱ የትውልድን ቀጣይነት እና ቅብብሎሽ ለማሳየት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
ኢሬቻ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ብሔራዊ ኩራት፣ ታሪክና ባህል የሚገለጽበት ታላቅ በዓል እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢሬቻ የእርቅ ፣ የሰላምና የአብሮነት መድረክ መሆኑን በመጥቀስ ሰላም በማውረድ በኩል ደግሞ ሴቶች ቀዳሚ በመሆናቸው ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ሀዳሲንቄዎች ‘መሬሆ’ ዞሮ መጣን፣’አራሮ’ እባክህ ታረቀን እያሉ ለፈጣሪ ምስጋና እና ውዳሴ እያቀረቡ ከፊት ይመራሉ ብለዋል።
በገዳ ስርዓት ውስጥ እናቶች ይከበራሉ አስታሪቂ ናቸው፣ በዚህ ምሳሌ ነው ሴቶች በኢሬቻ በዓል ላይ ከፊት የሚመሩት ይላሉ ሀዳሲንቄ ዘውዲቱ።
በገዳ ስርዓት አንድ አካል እና ነጸብራቅ የሆነው ኢሬቻ የፍቅር፣ የሰላም እና እርቅ በዓል በመሆኑ በእለቱ ሀዳሲንቄዎች ሰላም ያውጃሉ ብለዋል።
በዓሉ ሁሉም ያለምንም ልዮነት ብሔር፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ሳይገድበው የሚሳተፍበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሀዳሲንቄ ጫልቱ ኢብሳ በበኩላቸው የኢሬቻ ክብረ በዓል ብዙዎችን የሚያሰባስብ በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል ፈጣሪ በፈጠረው መልካ ላይ ከጭለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረን አምላክ ምስጋና የሚቀርብበት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን በጸደይ ወቅት ኢሬቻ መልካ በውሃ አካላት ዳርቻ እና በበልግ ወቅት ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ በተራራማ አካባቢ ይከበራል።