AMN-መስከረም 20/2017 ዓ.ም
ኢሬቻ የበለጠ እንዲያድግና ጎልብቶ እንዲታወቅ የዘርፉ ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ “ኢሬቻ ለባህል ህዳሴያችን” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ እንደተናገሩት ኢሬቻ የኦሮሞ ሀዝብ በጋራ የሚያከብረው ትልቁ በዓል ነው።
ኢሬቻ የገዳ ስርዓት ነፀብራቅ፤ የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና እና የአንድነቱ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህ ወቅትም ኢሬቻ በስፋት እና በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ገልፀው፤ በዓሉ የበለጠ እንዲያድግና ጎልብቶ እንዲታወቅ አሁንም ከምሁራን ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
በተለይም የዘርፉ ምሁራን የበዓሉን እሴቶችና መልካም ገጽታ የሚያጎሉ ስራዎችን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
‘ኢሬቻ መልካ’ ክረምቱ ወጥቶ የፀደይ ወቅት መግቢያ ላይ የሚከበር መሆኑን አንስተው፤ በዓሉ ትልቅ ፌስቲቫል እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የኢሬቻ ምንነትና ፋይዳ ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ ጽሁፍ እየቀረበ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።