ኢሬቻ – ፈጣሪ ለድንቅ ሥራው የሚመሰገንበት በዓል

You are currently viewing ኢሬቻ – ፈጣሪ ለድንቅ ሥራው የሚመሰገንበት በዓል

AMN – መስከረም 24/2017

“ኢሬቻ” ማለት ፈጣሪን (ዋቃ)ን ማመስገን ማለት ነው። ኢሬቻ ለምለም እና እርጥብ ሳር ተይዞ ፈጣሪ (ዋቃ) የሚመሰገንበት ሆኖ የበረከት፣ የመብዛት እና የመፍካት ሕይወትን የሚያመላክት ነው።

በዓሉ የምስጋና፣ የሰላም እና የይቅርታ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል። የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በንፁህ ልቦና ፈጣሪ ንፁህ ወዳደረገው የውኃ አካል ይኬዳል።

ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከክረምቱ የዝናብ፣ የብርድ እና የጨለማ ወቅት ወደ ብርሃናማው በጋ እንዲሁም ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው ፈጣሪው (ዋቃ) ምስጋና የሚያቀርብበት ትልቁ በዓሉ ነው።

በዓሉ መስከረም መጨረሻ ላይ የሚከበር ሲሆን የኦሮሞ ሕዝብም ፈጣሪ (ዋቃ) ለሰጠው በረከት እና ላደረገለት ምሕረት ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

ማኅበራዊ ደረጃ እና የዕድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር እንደቆየ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ማኅበረሰቡ ከየአካባቢው ተጠራርቶ በአካባቢው ወደሚገኝ ወንዝ (ውኃማ ስፍራ) በመትመም ለፈጣሪው (ዋቃ) ምስጋና ያቀርባል። እነዚህ የውኃ አካላት የተቀደሱ ናቸው ብሎም ያምናል።

በበዓሉ ላይ ከመቶ ሺዎች በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች፣ ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ ታዳሚዎች፣ ቱሪስቶች እና የተለየዩ የብሔረሰብ ተወካዮች ይሳተፋሉ።

በዋናነት አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ተሳታፊ ናቸው፡፡

በዓሉ በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እና በተለያዩ ሥርዓቶች ይከበራል። በተጨማሪም፣ የኦሮሞ ዳያስፖራ አባላት በሚገኙበት የተለያዩ የዓለም ሀገራትም ጭምር በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

በቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዲ እና በአዲስ አበባ ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓላት ላይ የሚሳተፉ ታዳሚያን እርጥብ ሳር በእጃቸው በመያዝ ወደ ሐይቁ ዳርቻ በመጠጋት ለምለሙን እና እርጥቡን ሳር በውኃ እየነከሩ ራሳቸው ላይ ይረጫሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ውኃ ውስጥ ገብተው ይጠመቃሉ።

ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል ሲሆን በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱ ይነገራል።

“ሆረ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓል ከ150 ዓመታት በፊት የዛሬዋ አዲስ አበባ በተቆረቆረችበት ስፍራ ሲከበር እንደቆየ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህ በዓል በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየ ሲሆን ከ150 ዓመታት በኋላ በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ዳግም በመዲናዋ መከበር ጀምሯል።

በጥቅሉ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ የደረሱ አዝዕርት፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ለመሰብሰብ ዝግጅት የሚያደርግበት እና በዚህም ሕዝቡ ደስታውን የሚገልጽበት ነው።

ኢሬቻ ፈጣሪ (ዋቃ) የሚመሰገንበት ብቻም ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ አዲሱን ብርሃናማ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት በመሆኑ ሁሉም ቤተሰቦች፣ ጓደኛማቾች እና ዘመድ አዝማድ ከያሉበት ተጠራርተው በአንድነት፣ በፍቅር እና በደስታ የሚያከብሩት በዓል ነው።

በበዓሉ ላይ ልጃገረዶች እና ጎረምሶች በባህላዊ ልብስ አጊጠው ባህላዊ ጭፈራ እያሳዩ ይደሰታሉ፤ የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖችን እየተቀባበሉ ያሰማሉ።

ሆ…ያ…መሬዎ…መሬዎ…“ፈጣሪን እናምናለን፤ በምድር ላይ የፈጠራቸውን ነገሮች ሁሉ እናደንቃለን” እያሉ ይህን ዜማ እየተቀባበሉ በማዜም ወደ ውሐው ስፍራ ይተማሉ፡፡

የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ባህላዊ ዜማዎች ያዜማሉ፤ በዚህም ለፈጣሪያቸው ምስጋናን ያቀርባሉ። በበዓሉ ላይ ወንድማማችነት፣ እርቅ እና ሰላምም ይንፀባረቅበታል።

ኢሬቻ ከበዓልነቱ ባለፈ በርካታ ቱሪስቶች የሚታደሙበት እንደመሆኑ የአገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ ይነገራል።

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review