AMN- መስከረም 22/2017 ዓ.ም
ኢሬቻ ፈጣሪ ለፍጥረታት ላደረገው ሁሉ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ሰላምና ወንድማማችነት የበለጠ የሚጠናከርበት በዓል መሆኑን አባገዳዎች ገለጹ።
በዓሉ በዋናነት በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ የሆራ ሃር-ሰዲ ከመስቀል በዓል በኋላ ባሉት ቅዳሜ እና እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በታደመበት ይከበራል።
የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር ቆይቷል።
የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው፤ ኢሬቻ።
ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር ቆይቷል።
ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።
የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔ በአዲስ አበባ እና ሆራ አርሰዲ በቢሾፍቱ ይከበራል።
በዓሉ በክረምትና በጨለማ የነበረው አስቸጋሪ ወራት ማለፉንና በጸደይ ጸሓይ ስትወጣና ብርሃን ሲታይ ምስጋና የሚቀርብበት ነው ይላሉ
አባገዳዎች።
በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል።
ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኘን ብሎ ምስጋና የሚያቀርብበትና ደስታውን የሚያንጸባርቅበት ወቅት እንደሆነ አባገዳ ዳውድ ዓሊ ተናግረዋል።
አባገዳ ዳውድ እንዳሉት ኢሬቻ የሚከበረው ፈጣሪ ለሰው ልጅ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና ለማቅረብ እና ወደ ፊት እንዲሆን ለሚፈለግ ነገር ለመማጸን ነው።
በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪ የፈጠረውን ለምለም ሳርና አደይ አበባ ይዞ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።
በዓሉ ላይ ያለምንም ልዩነት ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በጋራ የሚያከብረውና የህዝቦች ትስስር የሚጠናከርበት ነው ይላሉ አባገዳ ዳውድ።
የኦሮሞ ህዝብ ከባዱን የክረምት ወራት ያሳለፈውን ፈጣሪውን ወደ መልካ በመውረድ እንደሚያመሰግንና በንፁህ ልቦና ይቅርታን እንደሚጠይቅ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጸሃፊ አባገዳ አብዱራዛቅ አህመድ ተናግረዋል።
ዓመቱ የሠላም፣ የፍቅር፣ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆን ሰላም የሚሰበክበት በዓል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በዓሉን የሚታደም ማንኛውም ሰው ከቅርብ ሰው ጋር እንኳን ግጭት ከፈጠረ መጀመሪያ ከራሱም ሆነ ከሌላውም ሰው ጋር መታረቅ አለበት ብለዋል።
ይቅርባይነትና መመሰጋገን በማህበረሰብ ውስጥ እንዲኖር “ቂም ቋጥሮ ኢሬቻ ቦታ አይኬድም” ይላሉ።
ኢሬቻ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነትና ውበት የሚንጸባረቅበት መድረክ ነው ያሉት ደግሞ አባገዳ ደቻሳ ወዳጆ ናቸው።
ኢሬቻ የሰላም በዓል መሆኑን ከሚያመላክቱ ነገሮች ውስጥ የተጣላ ሰው እንዲታረቅና ሰላም እንዲሰፍን በሰው ልጆች መካከል ፍቅር እንዲሰፍን ማድረጉ ነው ብለዋል።
በዚህም ሰላምና መረጋጋት በህብረተሰብ ውስጥ እንዲሰፈን በማበረታት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን በጸደይ ወቅት ኢሬቻ መልካ በውሃ አካላት ዳርቻ እና በበልግ ወቅት ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ በተራራማ አካባቢ እንደሚከበር ኢዜአ ዘግቧል፡፡