ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮን (AUSSOM) ለማሳካት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

You are currently viewing ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮን (AUSSOM) ለማሳካት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮን (AUSSOM) ለማሳካት በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ከአንካራው ስምምነት በኋላ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ አልሸባብን በጋራ በመዋጋትና በቀጣናዊ ትብብር ዙሪያ ውጤታማ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ ልዑክ በሞቃዲሾ ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን አስታውቀዋል።

በውይይቱም ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ(AUSSOM) ስኬታማ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በአዲስ አበባ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር በሆነችው ጁቡቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝታቸውም ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በውይይታቸውም አልሸባብን በጋራ መከላከል፣ የነዳጅ መስመር ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ውጤቶችን ማስመዝገብ እና የሀገር ገጽታን ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ ማስተዋወቅ የሚያስችሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን እንግዶቿን እየተጠባበቀች መሆኑን ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review