የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ጉዳይ አስተባባሪ ልዑክ ጋር ግጭቶችን ለመከላከልና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት፤ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ ተቋማትና የተለያዩ ሴክተሮች ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በሚያጠናክር እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን በሚያፀና መልኩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው በመመለስ የተረጋጋ ሕይወትን እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሠራ ያለውን ሥራ አስመልክተውም ሚኒስትሩ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መከላከልና ሲፈጠሩም በሰላማዊ ውይይት መፍታት ሰፊ ጥረት የሚጠይቅ እና ልዩ ልዩ ባህሪያት ያለው በመሆኑ ከተለያዩ መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ጉዳዮች አስተባባሪ ዶ/ር ራሚስ አልካብሮቭ በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ ግጭትን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች አድንቀዋል።
እየተከናወኑ ያሉትን ግጭት የመከላከልና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፉ ቃል መግባታቸውንም ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።