ኢትዮጵያና ጀርመን በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ወልፍጋንግ ዶልድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ላላት ግንኙነት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጥ እና ጀርመን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት በፋይናንስ እና በቴክኒክ የምታደርገው ድጋፍ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር የምታደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን በውይይቱ ላይ አረጋግጠዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ወልፍጋንግ ዶልድ በበኩላቸው፤ የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በሰላም ማስከበር ዙሪያ የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን በውይይቱ ላይ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሁለቱን አገራት 120 ዓመታት የዘለቀ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የፖለቲካ ምክክር በማድረግ ወደ ሁሉን አቀፍ ትብብር ማሸጋገር በሚቻልበት አግባብ ላይም ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review