ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ላይ የማንለያይ መሆን አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህን ያሉት ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ባካሄዱት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ከጎበኙ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱም ወቅት ስለ ቀጠናዊ ሁኔታ፣ የፖለቲካ ምዕዳርና ስለ ሀገሪቱ ሰላም ጉዳይ፣ የትግራይ ክልልን የተመለከቱ ጉዳዮች እንደዚሁም የመልካም አስተዳደርና በልማት ስራዎች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ መንግስት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በየጊዜው ውይይት እያደረገ መሆኑን እውቅና ሰጥተው በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ ታሪክን መጠበቅ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ጉዳዮች እንደዚሁም ለኑሮና ለስራ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስለተሰራው የኮሪደር ልማት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የሀገሪቱን የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት፣ የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በሚፃረር ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አካላት፣ በሀገራዊ ምክር ሂደት ላይ እየተሳተፉ ያልሆኑ አካላትን፣ የፖለቲካ ምዕዳሩ ሁኔታና የመንግስት የሚዲያ ተቋማትን የተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ እንደዚሁም ዋጋ ንረት፣ ደሞዝ ጭማሪና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም (ዶ/ር) በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመገናኘት የተፈጠረው መድረክ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚተባበሩ መሆናቸው ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ጠቅሰው የተፈጠረው መድረክ በራሱ ምህዳሩ እየሰፋ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓመት ሁለቴ ሶስቴ ፓርቲዎችን ሰብስቦ አያናግርም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸው ይህን የሚያደርገው በውስጡ ያለውን ክፍተት ለማየት ከፓርቲዎች የሚያገኘው ሀሳብ ጠቃሚ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የብልፅግና ዕሳቤ በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፉክክር ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግም ነው ያስረዱት፡፡ አክለውም ፍጹም የሆነ የፖለቲክ ምህዳር መጠበቅ ማለት ፖለቲካን አለመረዳት መሆኑን አውስተው፣ በመንግሥት በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጥረት አየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ጤናማ የሆነ ፉክክር እና ትብብር ሲኖር ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደሚሰፋ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ 273 የተፎካካሪ ፓርቲ ሰዎች በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ተወክለው እየሠሩ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከነዚህም ውስጥ አራት ሚኒስትሮች፣ አራት ሚኒስትር ዴኤታዎች እና በርካታ የቢሮ ኃላፊዎች እስከ ዞን ድረስ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ “እነዚህን ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በአስተዳደሩ ውስጥ አሳትፋለሁ ያለ መንግሥት ለትብብር ያለው ቦታ ትልቅ እንደሆነ ማሳያ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ እና ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ በጋራ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የትጥቅ እና ሰላማዊ ትግልን ቀላቅሎ መንቀሳቀስ እንደሚስተዋል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ፓርቲዎች ብቸኛው ኃይልን የመጠቀም ሥልጣን የመንግሥት መሆኑን ተቀብለው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ “ከሥጋው እፆማለሁ ከመረቁ አድርጉልኝ” የሚል አባባልን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ሰው ከጾመ ከሥጋውም ከመረቁም እንደሆነ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሰላም እና የትጥቅ አካሄድን አጃምለው መንቀሳቀስ የለባቸውም ብለዋል፡፡
“የፖሊሲ ልዩነት ቢኖረንም በኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያን በመገንባት እምብዛም የማንለያይ መሆን አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኃይል ፍላጎታችንን እናስፈጽማለን ማለት ግን ይህን አካሄድ ያበላሻል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ምርጫ የተሻለ አካታችነት ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ፣ የተሻለ ነገር እንዲመጣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው ኃይላቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡ ብልፅግና በምርጫው ማሸነፍን ዓላማ አድርጎ ይሠራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ጠቅላይነት እንደማያዋጣ እና አካታች የፖለቲካ መድረክ በኢትዮጵያ ውስጥ እውን መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምኑም አውስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የትግራይ ክልልን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ሊመጣ የሚገባው ልማት፣ ሊሰራ የሚገባው ስራ በበቂ ተሰርቷል ብለን አናምንም ያሉ ሲሆን የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስን በሚመለከት መቶ በመቶ ዝግጁ ነበርን፣ አሁንም ነን ብለዋል። ከዚህ በፊት ራያ ላይ የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለስ ስራ መሰራቱን እና በወልቃይትም በተመሳሳይ ከጊዜያዊ መንግስቱ ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ዜጎች ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ሳይሆኑ ቦታቸው ቢመለሱ ከማንም በላይ ኢትዮጵያ ታተርፋለች ሲሉ ተናግረዋል።
ከሕገ መንግሥት ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ሕገ መንግሥት ካልተቀየረ ምኑን የለውጥ መንግሥት ይባላል የሚል እሳቤ ሕፀፅ ያለበት ነው” ያሉ ሲሆን ጥያቄው ተመልሶ ቢፈተሽ የተሻለ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ለውጥ ሕጎችን፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ መመሪያዎችን ሊይዝ ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕገ መንግሥትን መቀየር ብቻ ለውጥ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ መታረም ያለበት ቦታ ላይ በጋራ በመሆን ማረም እንደሚያስፈልግም ገልጸው ለዚህ የሚሆን መድረክ መፈጠሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን አሁንም በመድረኩ ለመጠቀም ዳተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የማይነሳ ጉዳይ እንደሌለ ጠቅሰው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዳተኛ ከመሆን ይልቅ ቀረ የሚሉትን ሀሳብ መስጠት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚስተዋለው የሰላም ችግር መፍትሄው ምንድነው? ለሚሉ ጉዳዮች በሰጡት ምላሽ መንሥኤው ፍላጎትን በኃይል የማስፈፀም ኋላቀር እሳቤ ነው ብለዋል፡፡ በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን በጉልበት ለማስፈፀም የሚደረገው ጥረትና ሙከራ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ገልፀዋል። የተለየ ሀሳብ ያለው ሁሉ የግድ ወደ ውጊያ ከመግባት ሀሳቡን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማራመድ የሚችልበት ምህዳር በመኖሩ መጠቀም ይችላል፤ ጉልበት የመጠቀም እሳቤን በጋራ ማስቆም ያስፈልጋል ብለዋል።
አንዳንዶች ለብዙ ሀገራት ተቀጣሪ ባንዳ በመሆን የሀገር ብሔራዊ ጥቅም በሚጋፋ መልኩ የመሪው አልጋው አልፀናም በመነቅነቅ እናባርረው በሚል ከጠላት ጋር እየሰሩ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የህዝቦችን መብት እንደሽፋን በመጠቀም የፖለቲካ ንግድ የሚሰሩ፤ እንታገልለታለን የሚሉትን ህብረተሰብ ክፍል የሚያግቱ፣ የሚዘርፉ፣ የሚገሉ መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ለአብነትም ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት እየታገልን ነው እያሉ ህዝቡን እያገቱ እያሰቃዩ በህብረተሰብ ስም የፖለቲካ ንግድ የሚሰሩ መኖራቸውን አንስተዋል።
እርስ በእርሳቸው የማይስማሙ ሃይሎች በታጋይ ስም ተደራጅው ዘረፋ ይፈፅማሉ፤ በህዝበኝነት ስም የተገነቡ ትምህርት ቤቶችን ያፈርሳሉ፣ አስተማሪዎችን ያግታሉ፣ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደር እንዳይደርስ መንገድ ይዘጋሉ ብለዋል። ይህም በኢትዮጵያ ህዝበኝነትና ህዝባዊነት ድንበራቸውን ስተው መቀላቀላቸውን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎትን በጉልበት ለመፈፀም ያለውን የተሳሳተ እሳቤ ለመግራት መንግስትም ራሱን ይፈትሻል እናንተም ውስጣችሁን ፈትሹ ሲሉ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ኃላፊነት ሰጥተዋል።
የባህር በርን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን የህልውናዋ ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መልማት መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ ሰላም መሆንና መልማት ለቀጣናው ዕድገት በጎ ሚና እንደሚጫወትም ጨምረው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እና ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም እና ልማት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ ጎረቤቶቿ ሊረዱ እንደሚገባ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሰራች እንደምትገኝም ተናግረዋል። የባህር በር አለመኖር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝም ገልጸው ጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያሻው አሳስበዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት እና ይህም በንግድ ህጎች አማካኝነት ምላሽ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በቀናነት እንዲረዱትና ጥያቄው ከመልማት እና ከማደግ ካለ ጽኑ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ለውጡ ከመምጣቱ በፊት በነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት ፓርቲዎች አጋር እና ዋና ተብለው የተለዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ ግን ይህን አካሄድ እንደቀየረ ተናግረዋል። እንደ ምርጫ ቦርድ እና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ መደረጋቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ላስተዋለ አካል ይህ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት በነጻነት እንዲሠሩ ጣልቃ እንደማይገባ ጠቁመው፣ “የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በርካታ ሪፖርቶችን እኛ ላይ ሲያወጣ ይህም ልምምድ መሆን አለበት ብለን ምንም አላልንም” ብለዋል፡፡ ለውጡ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፍም በግልጽ እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ያለው መንግሥት ትላንት የተሠሩ መልካም ነገሮችን ሁሉ አሳምሮ በማስቀጠል እንደሚያምን በቅርሶች እድሳት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ማሳያ እንደሆነ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም የእውነተኛ ለውጥ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ለውጥ መምጣቱን አንስተው የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ዓመት በግማሽ ስለመቀነሱ ተናግረዋል። ይህንንም ለማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከፍተኛ ድጎማ ማድረግ እና የንግድ ስርዓቱን የማዘመን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሰሞኑን ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከመምህራን፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያ ተወካዮችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ