አዲስ ሚዲያ ኔትዎርከ( ኤ ኤም ኤን )መስከረም 7/2016 ዓ.ም
ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀብት እንዳይባክንና ሌብነትን በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ጥላሁን ከበደ፤ ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ለበርካታ ዓመታት ተጠራቅሞ የመጣ የዕዳ ቀንበር ተጭኗት መቆየቱን አንስተዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ይህንን የዕዳ ጫና በየደረጃው ቀንሶ ለሀገር ምንዳን ለማትረፍ ውስጣዊ ፀጋን፣ አቅምንና የተፈጥሮ ሀብትን ጠንቅቆ ማወቅ የቅድሚያ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ባለው ስልጠና በተለይ አመራሩ የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች በአግባቡ ለይቶ በማወቅ ለማልማትና የሀብት ብክነት እንዳይኖር በቁጭት እንዲነሳ ማድረግ ዋና ዓላማው መሆኑን ገልጸዋል።
በፋብሪካዎች ባደረጉት ጉብኝትም የተፈጥሮ ጸጋን በአግባቡ እሴት ጨምሮ ከራስ አልፎ ለሀገር እንዴት መትረፍ እንደሚቻል የተመለከትንበት ነው ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን ለሁሉም ዜጎች የምትመች ሀገር አድርጎ በመገንባት በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ተግቶ መስራት፣ ሌብነትን በቁርጠኝነት በመታገል የሀብት ብክነት እንዳይኖር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ የውሃ ሀብት፣ ትልቅ አምራች የህዝብ ቁጥር ቢኖራትም አሁንም በርካታ ህዝብ በድህነት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ሳይታረስ ጦሙን የሚያድር መሬትን ወደ ልማት የማስገባት፣ የውሃ ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም፣ ማዕድናትን የማልማት ስራን ጨምሮ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የታቀዱ የልማት ስራዎችን በአዲስ አስተሳሰብ በፍጥነትና በጥራት ለማሳካት እንሰራለን ያሉት አቶ አሻድሊ፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ ችግሮችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም አሟጦ በመጠቀም ለውጥን ማረጋገጥ እንደሚቻል ከስልጠናው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በየዘርፉ ሀብት መፍጠር እንደሚገባና የሚባክን ሀብት እንዳይኖር በማድረግ ከሀገር ፍጆታ አልፎ ለሌላው ዓለም መትረፍ እንደሚቻልም በንድፈ ሀሳብና በተግባር’ ማየታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ያሉ ጅምሮችን አጠናክሮ ድህነትን ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ ሀገርና ህዝብን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገርም አመራሩ ተጨማሪ ሀብት ለሀገር የመፍጠርና በአግባቡ የማስተዳደር ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አስረድተዋል።
ስልጠናው አመራሩ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንዲሰራ አቅም የሚፈጥር ነው ያሉት የፓርቲው አመራርና በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኤልያስ ገዳሙ ናቸው።
ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን ጫና የተሻገረችው በህዝብና በአመራሩ የተቀናጀ ትግል መሆኑን በማንሳት፤ በቀጣይም ፈጣን ልማትን ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜና የበጀት ዕቅድ በአግባቡ ፈፅሞ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ሀብት እንዳይባክን፣ ሌብነትን መጠየፍና መቆጣጠርም የአመራሩ ቀጣይ የቤት ስራ ነው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል የወሳኝ ኩነት ቢሮ ኃላፊና የፓርቲው አመራር ወይዘሮ ዛሃራ ሰሚር በኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በርካታ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቃ መቆየቷን አስታውሰው፤ አሁን ያለው አመራር ዕዳዋን አቃልሎ ሀገርን ለማሻገር ስልጠናው ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ሲሉ አክለዋል።
ሀብት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያህል እንዳይባክን ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግም የአመራሩ ወሳኝ ሚና ነው ያሉት ወይዘሮ ዛሃራ፤ ለህብረተሰብና ለሀገር ለውጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፤ ስልጠናው የብልጽግና ፓርቲ ለህዝቡ የገባውን ቃል ማስፈፀም የሚያስችል የአመራር አቅም የመፍጠር ዓላማን የሰነቀ መሆኑን በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ መግለፃቸው ይታወቃል።
ፓርቲው ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋጥ በሚያደርገው ጥረት በተለይም የአመራሩ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ወሳኝ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr
Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9
Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8
Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ