ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ለሰላም ሊተጉ ይገባል – የሀይማኖት አባቶች

You are currently viewing ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ለሰላም ሊተጉ ይገባል – የሀይማኖት አባቶች

AMN – ጳጉሜን 4 /2016 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የመደጋገፍና የአብሮነት እሴትን በማጎልበት ለሰላም ሊተጉ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሀይማኖት አባቶች የህብር ቀንን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅና የባህርዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሀም አዲሱ ዓመት ሁሉም ለሰላም በመቆም ፈጣሪ የሚወደውን ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት እንዲሁም ለመደጋገፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል በንሰሃ ያለፈውን ይቅር በማለት ለሚመጣውም የፈጣሪን ፈቃድ ለመፈጸም መነሳሳት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ የሁላችንንም ፍላጎት ሰላም፣ ደስታ፣ ፍቅርና አንድነት ነው ብለዋል።

የየትኛውም እምነት ተከታዮች ሰላምን ምርጫ በማድረግ ለሰላምና ለአብሮነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የቤተሰብ፣ የምእመናንና የወጣቶች ሀዋሪያዊ አገልግሎት ዳይሬክተር አባ አብነት አበበ በበኩላቸው አዲሱን ዓመት ለሰላምና ለአንድነት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለአብሮነትና ለአንድነት ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ የምንቀበለው ዓመት እርስ በእርስ ተከባብረን ይቅር ተባብለን መሆን አለበት ብለዋል።

አዲሱ ዓመት አንዱ ለአንዱ የፈውስ ምክንያት ሆኖ የሚኖርበት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ በምንቀበለው ዓመት ለሀገር እና ለህዝብ መልካም ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል።

እንዲሁም አገራችንን የምናገለግልበትና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሰላም የምንቆምበት መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛ ያለፈውን በመተው ክፉ ሀሳብን በማስወገድ ራስን በማረቅ መልካምነትን መላበስ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከጸሎት ባለፈ ፈጣሪ የሰጠንን ሰላም ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ሲሉም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ-ክርስትያን ዋና ጸሀፊ ስምኦን ሙላቱ(ዶ/ር) ለተጨመረልን ዓመት ፈጣሪን እያመሰገንን ክፋትና ተንኮልን በማስወገድ መሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

በሚያልፍ ዘመን ክፋት ምቀኝነትን ሳይሆን ፈጣሪ የሚወደውን ተግባር እየፈጸምን ልንኖር ይገባል ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review