AMN – መስከረም 28/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በመጀመሪያው የዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ ተሳትፏቸው የብር ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡
በሩሲያ ሶች ግዛት ሲሪየስ ከተማ በተከናወነው ዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡
በውድድሩ ኢትዮጵያን በመወከል በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት ስር በተደራጀው የኢትዮጵያ ልጆች የስፔስ ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል ላለፉት 4 ዓመታት በክረምት ወራት ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ 5 ታዳጊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መካከል ተማሪ ፍትሕ ግርማ የብር ሜዳሊያ፣ ተማሪ ሚካኤል አሸናፊ እና ተማሪ አላዛር አዳነ እያንዳንዳቸው የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኙ ተማሪ ሙሳ ከድር ደግሞ የብርቱ ተወዳዳሪ የክብር ሽልማት አግኝቷል፡፡
ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡