AMN- መስከረም 30/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ሃይማኖቶችን ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረጓ እና በእንግዳ አቀባበል ያላት ታሪካዊ ቅርስ ለሁሉም ኩራት ነው ሲሉ የሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ገለጹ፡፡
በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሞሮኮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን ከሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ ጋር ተወያይቷል።
የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት የሞሮኮ ሕዝብ በባህልና በሃይማኖት ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰላል፡፡
እነዚህ ዕሴቶች በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የነቢዩ መሐመድ ባልደረቦችና ቤተሰቦችን በዚያ ፈታኝ ወቅት በማስተናገድ የዋለችው ውለታ በሙስሊሙ ዓለም ታሪክ በደማቁ የተጻፈ መሆኑን ገልጸው ሀገሪቱ በመላው ሙስሊሙ ልብ ውስጥ ያለች ሀገር መሆኑንም ተናግረዋል::
በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የታሪክና የሃይማኖት ግንኙነት ለማጠናከር የሚኒስቴር መ/ቤታቸው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የሁለቱ ሀገራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የልምድ ልውውጥ መድኮችን ለማከናወን በሞሮኮ ይፋዊ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል::