AMN – መስከረም 21/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በተለይም በቀንዱ አገራት ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቷን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሰኒ ሮግስትሩፕ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ በአለም አቀፍና አህጉራዊ መድረክ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ዘርዝረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና ጸጥታን በማስከበር ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳላት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር በቀጣናዊ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እኤአ በ1951 በኮሪያ ጦርነት ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተመራው ሃይል የነበራትን ወሳኝ ተሳትፎ አስታውሰዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ጸጥታ መከበር ላበረከተችው አስተዋጽኦ በታሪክ የተመዘገበ ጉልህ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለሰላም መከበር ያላት ቁርጠኝነት በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በተግባር የተረጋገጠ እንደሆነ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
በምስራቅ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ውጥረት በመፍታት ሰላምን ለማምጣት ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና እንደምትጫወትም እምነታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ዴንማርክ በሰላምና ጸጥታ አጀንዳዎች ዙሪያ ከአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ቀጣናዊ ተቋማት ጋር ያላትን የቆየ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰላምና በንግግር በመፍታት ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የጎላ ሚና ተጫውታለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና የሚያጋጥሙ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ሚናዋን በመወጣት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አበርክቶ አላት ነው ያሉት።