የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የአለም ጤና ደህንነትን እና የወረርሽኝ ዝግጁነት ማጠናከር ዙሪያ የእንግሊዝ ልኡካንን አነጋግረዋል።
ስብሰባው በጤና ስርዓት፣ በወረርሽኝ ምላሽ እና በሰው ሃብት ልማት የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር ላይ ያተኮረ እንደነበር የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
የዩናይትድ ኪንግደም የልዑካን ቡድን በአፍሪካ ግሎባል ጤና ቡድን መሪ በዶ/ር ኡዞአማካ ጊልፒን የተመራ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም ወረርሽኝ ስምምነት ድርድር ቡድን ቁልፍ አባል የሆኑትን ሚስተር ቶም ስቶሪ አንጀልን ያካተተ እንደነበር ተገልጿል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ ፣ ኢትዮጵያ ለወደፊት የጤና ድንገተኛ አደጋዎች የተሻለ ምላሽ ለመስጠት ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማስመዝገብ እና የጤና ስርዓቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አጉልተዋል።
ከእንግሊዝ ጋር ያለን አጋርነት በጤና ደኅንነት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ ተቋቋሚ የጤና ስርዓትን በመገንባት እና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር መቅደስ አክለዋል።
ዶ/ር ኡዞአማካ ጊልፒን ፣ ኢትዮጵያ በጤና ስርአት ማሻሻያ ሂደት እያስመዘገበች ያለችውን እድገት አድንቀው እንግሊዝ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የጤና ደህንነት ላይ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።