AMN – የካቲት 7/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ስኬታማ ተሳተፎ ያደረገችበት የአለም መንግስታት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ “ሀገራችን ኢትዮጵያ በተግዳሮት የማይናወጥ ቋሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ማህበራዊ ዋስትና እና ጠንካራ መንግስታዊ አስተዳደርን መገንባቷን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ስልታዊ አይበገሬነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በማመን ሀገር በቀል በሆነው የመደመር እሳቤ ተመርታ ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ ውጤታማ” መሆኑን አስረድተዋል።
ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል፣ ማህበራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለመፍጠር ጠንካራ የመንግስት አስተዳደር ስርዓቶችን አስፈላጊነት የሚያጎላው ጉባኤ ‘የወደፊት መንግስታትን መቅረጽ’ በሚል መሪ ቃል በፈረንጆቹ ከየካቲት 4 እስከ 6 ቀን 2017 በዱባይ ሲካሄድ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን አቶ አደም ፋራህ በተጨማሪ የግብርና ሚኒስትሩን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)ን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ነበር።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ውጤታማ ፖሊሲ ማውጣት፣ የዜጎች ተሳትፎ፣ ዘላቂ ልማት፣ የውሃና መስኖ አጠቃቀም እና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከቱ ከፍተኛ ደረጃ መድረኮች፣ የፓናል ውይይቶች እና መስተጋብራዊ ኩነቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።
የመንግስት ተወካዮች ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከሌሎች አገራት አቻዎቻቸው እና የአለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በአለም መንግስታት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያሳየችው ንቁ ተሳትፎ ለአለም አቀፍ ትብብር እና ለዘላቂ ልማት ጥረቶች ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በተጨማሪም ጉባኤው ኢትዮጵያ ስትራቴጅካዊ አጋርነቶችን ለመገንባት፣ እውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ እና ከሌሎች ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ያስቻላት እንደሆነ አንስተው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ለማምጣት እያሳየች ላለችው ቁርጠኝነት ተጨማሪ ድጋፍም አስገኝቶላታል ብለዋል።
ለሶስት ቀናት በተካሄደው የአለም መንግስታት ጉባኤ ከ25 በላይ የሀገር መሪዎች፣ 150 በላይ የመንግስት ልዑካን፣ ከ80 በላይ አለም አቀፍ እና ክልላዊ ድርጅቶች እና ተቋማት፣ ባለሙያዎች እና ከ3 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መታደማቸውን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።