ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የታደለች ሀገር ናት- አቶ ሞገስ ባልቻ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የታደለች ሀገር ናት- አቶ ሞገስ ባልቻ

AMN – መስከረም 21/2017 ዓ.ም

የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” ባህላዊ ትውፊቱን በሚያጎሉ የተለያዩ ትዕይንቶች እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እና ሌሎች የፌዴራልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ሄቦ ” የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ፡ የህብር ኢትዮጵያ ድምቀት” ነው ብለዋል፡፡

“ህብር ተፈጥሯችን ውበታችንም ድምቀታችንም ነው” ያሉት ኃላፊው ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የታደለች ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።“መልከዓ ምድራችን ጭምር የህብር ማንነታችን ነፀብራቅ ነው” ሲሉም አስፍረዋል::

“ከህብረብሔራዊቷ አዲስ አበባ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ብንጓዝ የኢትዮጵያን ህብር ስሪት እናገኛለንም” ብለዋል።

“አቅጣጫችን ወደ ጅማ መስመር አድርገን ነፋሻማውን አየር እየማግን በጠዋቱ ስልጣኔም እንደ ወንዙ ጅረት ከፈሰሰበት ከጊቤ ወንዝ አካባቢ ተከስተናል” ሲሉም አስፍረዋል።

የአዲስ ዓመት ብስራት የሆነው መስከረም ወር ተፈጥሮው ልምላሜ መሆኑን በመግለጽ የበርካታ የሀገራችን ብሔረሰቦችም የዘመን መለወጫ በዓላት የሚከበሩበት እንደመሆኑ የተለየ ድምቀት እንዳለው ኃላፊው ጠቁመዋል።

ከጊቤ ባሻገርም የታሪክ እና የባህል ሀብታም የሆነው በውብ የተፈጥሮ መስህብ የተዋበው የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ሄቦ የሚከበርበት ወቅት እንደመሆኑ ይበልጥ መድመቁን ነው የገለጹት።

“ጥቅጥቅ ጥብቅ ደኖች ፣ በጥበብ እጆች የተሳሉ የሚመስሉ ውብ ተራራዎችና ኮረብታዎች ፣ ከአዝመራው እሸት ጋር ተደማምሮ መአዛው ያውዳል” ሲሉም ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review