
AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያሳይ መካነ ርዕይ (ፓቪሊየን) በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተመርቆ ተከፍቷል።
ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥና በረሀማነትን ለመከላከል እየሰሩ ያሉትን ስራ በሚያቀርቡበት አለም አቀፍ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያሳይ መካነ ርዕይ ክፍት አድርጋለች።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል፣ በዘላቂ ግብርና እና በደን ጥበቃ ላይ ያላትን አዳዲስ አቀራረቦች ያነሱት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብን ለመገንባት ቁርጠኛ ነች ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አለም ትኩረቱን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በማድረግ ተጨባጭ ድጋፎችን በተለይ ለታዳጊ ሀገራት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።
አክለውም ዓለም አቀፍ ትብብር በማድረግ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ መፍትሄዎችን በማምጣት ረገድ
አለም አቀፍ ትብብሩ ያለውን ወሳኝ ሚና ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ ( ዶ/ር/ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል አቅርቦት በምግብ ዋስትና እና በቱሪዝም መዳረሻ ስራዎቿ እንዲሁም የችግኝ ተከላ እና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን ያስቀደመ ስራ እየሰራች ነው ብለዋል።
ዘንድሮ በአዘርባጃን፤ ባኩ በተጀመረው የኮፕ 29 እየተሳተፈ ያለዉ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ቁልፍ ውይይቶችን በማድረግ የኢትዮጵያን የአረንጋዴ አሻራ እና አካባቢ ጥበቃ ተሞክሮ ያካፍላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።