AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የአፍሪካን የአቪዬሽን ዘርፍ እንድትመራ ያስቻሉ ጠንካራ ተቋማት መገንባቷን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የበዓሉ አከባበር የፓናል ውይይት፣ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
ፖቴዝ_25 የተሰኘችው አውሮፕላን በፈረንጆቹ 1929 ከጅቡቲ ተነስታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር ላይ በመንሳፈፍ ገፈርሳ አካባቢ ስታርፍ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ እንደተጀመረ ታሪክ ይናገራል።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 7 ቀን 1944፤ በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ በተካሄደ ጉባኤ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሲቋቋም አፍሪካን ወክለው ከተገኙ ሶስት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መመስረትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በተለያዩ ጊዜያት በወጡ የማቋቋሚያ ህጎች አደረጃጀትና ኃላፊነቱን ሲያሻሽል ቆይቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያስመዘገባቸው ካሉ ስኬቶች ጀርባ ጠንካራ ደጀን የሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም መኖሩ ጠንካራና ስመ ጥር አየር መንገድ እንዲኖረን አድርጓልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በቀዳሚነት የምትመራ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉንም ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከበርካታ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት መፈራረሙን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፋዊ መዳረሻዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ጠቅሰዋል።
ባለስልጣኑ የኤርፖርቶች ግንባታና ቁጥጥር ሂደትን የማስተዳደር ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ባካሄደው ለውጥ የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች 23 የደረሱ ሲሆን አራቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን ማሟላታቸውን ጠቅሰዋል።
አውሮፕላኖችን በመመዝገብ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ፣ ለአብራሪዎች፣ ለቴክኒሻኖችና ለአስተናጋጆች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠት፣ የማሠልጠኛና የጥገና ተቋማትን ፈቃድ እና ሌሎች ተግባራትን በብቃት እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።