ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭ የሆነችባቸው የዲፕሎማሲ ድሎች
AMN – ጥር 25/2017 ዓ.ም
1.የአንካራው ሥምምነት
የአንካራው ሥምምነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ድል ካስመዘገበችባቸው መድረኮች አንዱ እና በአለም መድረክ በዲፕሎማሲው ረገድ በተሰራው ስራ የተገኘ ስኬት ነው።
ሥምምነቱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተመዘገበበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም መረጋጋትን ፈጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ከሶማሊያ ጋር የነበረውን አለመግባባት ተጠቅመው የኢትዮጵያን የውሥጥ እና ውጫዊ የሠላም እና ልማት እንቅሥቃሴዎችን ለማወክ ለቋመጡ ኃይሎች ኪሣራ እና ድንጋጤን ጥሎም አልፏል፡፡
2.የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል
ብሪክስ ሌላኛው የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ድል የተመዘገበበት የዲፕሎማሲው መድረክ ስኬት ነው።
ብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ከፍ ማድረጊያ መሳሪያ እና በአለም አቀፍ አስተዳደር ላይ ሚዛን ለመጠበቅ ያለመ እንደሆነ ይነገራል።
አባል ሀገራቱ ከዓለም ህዝብ 45 በመቶውን የሚሸፍኑ ሲሆን 28 በመቶ የሚጠጋውንም የአለም ኢኮኖሚም እንደሚይዙ ዘኢኮኖሚስት የብሪክስ አባል ሀገራት እና የዓለም መሪዎች በሩሲያ፣ ካዛን ኤክስፖ ማዕከል ያደረጉትን ስብሰባ አስመልክቶ ባስነበበው መረጃ ጠቅሷል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አባል ሀገራቱ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ብሪክስ እኩልነት የነገሰባትን አለም ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው በመገንዘብ የተሰራው የዲፕሎማሲ ስራ ውጤት ነው።
3.ለኮንፍረንሶች ተመራጭ የሆነች ከተማ – አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥሎ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደሆነች ለዓመታት ሲነገር የቆየ ሀቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገዷ ሀገሪቷ ዲፕሎማሲዋ የደረሰበትን ከፍታ እንደሚያሳይ እና ኢኮኖሚዋ እንዲነቃቃና እድገት እንዲያሳይ ፣ አለምአቀፋዊ መገለጫ የሆኑትን ባህልና እሴቶቿን ለማስተዋወቅ ፣መሰረተ ልማቶቿን ለማዘመን እና የባህል ልውውጥ ለማድረግም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በያዝነው አመት ብቻ መዲናችን አዲስ አበባ ወደ 30 የሚጠጉ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎችን በስኬትና በድምቀት አስተናግዳለች ፡፡
ካስተናገደቻቸው አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ስብሰባዎች ውስጥም (World Without Hunger) ከረኅብ ነጻ የተሰኘው አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ተጠቃሽ ሲሆን ይህ ኮንፈረንስ ረሃብን ለማጥፋት እና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ያለመ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች እና እቅዶች ላይ አተኩሮ የመከረ መድረክ ነበር።
በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዙሪያ የመከረው የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ፣ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበር ጉባኤ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባኤ፣ ዓለምአቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ኮንፈረንስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት (UNIDO) ጉባኤ፣ የዩኒስኮ (UNESCO) በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መከላከል ቀን መታሰቢያ እና ሌሎችም በርካታ መድረኮች በአዲስ አበባ መካሄድ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው የዲፕሎማሲ ድሎች አካል ተደርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በአንድ ወቅት አዲስ አበባ በውበቷና በመሰረተ ልማት ወደኋላ የቀረች በመሆኗ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችን ለማስተናገድ አትመጥንም ተብላ የተዘመተባት ከተማ በተሰራው የኮሪደር ልማት ሥራ ሌሎች ሀገራት በዓመታት ውስጥ እንኳን ለማዘጋጀት የማይችሉትን ትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በተሳካና በደማቅ ሁኔታ ለማስተናገድ መብቅቷ ሀገሪቱ የደረሰችበትን ዓለምአቀፍ ኹነቶች የከተማይቱን ብሎም የሀገሪቱን ገጽታ አጉልተው የሚያሳይ የዲፕሎማሲ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡
እነኚህ ሁሉ የሀገሪቱን ገጽታዎች የቀየሩ ድሎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የተመዘገቡ የዲፕሎማሲው መድረክ ስኬቶች ናቸው።
በወርቅነህ አቢዮ