
AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ውጤታማ ተግባር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን “ከረሀብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባኤ የተሳተፉ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አፍሪካውያን ባለሃብቶች ገለፁ።
“ከረሀብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
አፍሪካውያን የግብርና ዘርፍ ኢንቨስተሮች እንዳሉት ጉባኤው ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ካለው ስራ ልምድ ለመቅሰም አስችሏቸዋል።
የአፍሪ ፉድስ ዋና ዳይሬክተር ካኪና ሁሴንጂማና በሩዋንዳ የሚገኘው ድርጅታቸው ምግብና አትክልቶችን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡
ድርጅታቸው በአገሪቱ ካሉ 4ሺህ ወጣት አርሶ አደሮች ጋር በግብርናና እንስሳት ልማት በትብብር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የተደረገው ጉባኤ ለአለም በተለይ ደግሞ በችግር እየተፈተነች ላለችው አፍሪካ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
በካሜሮን የሚገኘው ቴልካር ኮኮዋ ድርጅት የደንበኞች አገልግሎት አስተባባሪ አልበርት ቬጋህ በበኩላቸው ድርጅታቸው የካካዋ ምርትን ከአርሶ አደሮች በመረከብ ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛችና በነፃነት የኖረች አገር ከመሆኗ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በግብርናና ሌሎች ዘርፎች በራሷ አቅም ባከናወነችው የልማት ስራ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በግብርና እየተገኘ ያለው ምርት ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑና ኢትዮጵያ በዚህ በኩል እየሰራች ያለው ስራ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረትና እያደረገ ያለው ድጋፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማስቻሉን በኮንፍረንሱ ከተደረገላቸው ገለፃ መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።
ለአርሶ አደሮች የግብርና ሙያ ስልጠናና የቴክኖሎጂ ግብዓት በማቅረብ በትብብር እየሰሩ መሆኑን የገለፁት በናይጄሪያ በግብርና ቴክኖሎጂ ላይ እየሰራ የሚገኘው የፋርም ፊክሰርስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ታያኦ ኦላኡንፓኩን ናቸው።
ኢትዮጵያ በተለይ በቡና ምርቷ የምትታወቅ መሆኗንና የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ረሃብን ለማጥፋት አፍሪካ ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባት ገልፀው የሚያሰራ የህግ ማዕቀፍ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመጠቀም የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአፍሪካ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንግስት፣ አርሶ አደሩና ባለሃብቶች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ገልፀዋል።
አገራት እርስ በርስ ያላቸውን የመሰረተ ልማት ትስስር በማጠናከርና ባሉ አህጉር አቀፍና ቀጣናዊ ማዕቀፎች በመጠቀም የንግድ ትስስራቸውን ማጎልበት እንዳለባቸውም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።