AMN- መስከረም 9/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ በሚቀጥለው ሳምንት ማብቂያ በኒውዮርክ በሚካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሀገራዊ ተሳትፎ ከወዲሁ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
193 አባል ሀገራትን የሚያሳትፈው ጉባዔው ዓለምአቀፍና ቀጠናዊ ሁኔታዎች በጥልቀት እንደሚመክሩበት ይጠበቃል።
በዚህ ጉባዔም ለ79 ዓመታት ያልተቋረጠ ተሳትፎ ያላት ኢትዮጵያ ሁነቱን ብሄራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ እንደምትጠቀምበት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብያት ጠቁመዋል።
ጉባዔው በርካታ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እንዲሁም በባለብዙ ወገን የትብብር ዘርፎች ያላትን አጋርነት ለማጠናከር በንቃት እንደምትንቀሳቀስም ገልፀዋል።
ከጉባዔው ተሳትፎ ጎን ለጎንም ከሀገራት እንዲሁም ከልማት ድርጅቶች ጋርም ምክክሮችን ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት መጠናቀቁንም አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ከመጪው መስከረም 14 እስከ 20 2017 ድረስ በአሜሪካ ኒውዮርክ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
በአቡ ቻሌ