ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ከሁሉም ጋር በትብብር ትሰራለች – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ከሁሉም ጋር በትብብር ትሰራለች – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

AMN-ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያረጋግጡ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ከሁሉም ጋር በትብብር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከሚገኙ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ተወካዮች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ረጅም የመንግሥት ታሪክ ያላት ጥንታዊት አፍሪካዊት ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ በመከተል የነገን ብሩህ ተስፋ የሰነቀች ሀገር መሆኗንም አብራርተዋል።

በመሆኑም በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላትን የጎላ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤትና የወጣቶች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ እነዚህን ዕድሎች በመጠቀም ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ማደግን መሰረት ያደረገ መርህ በመከተል በቀጣናው የመሪነት ሚናዋን እንደምትወጣም ተናግረዋል።

በኢጋድ ያላትን ስትራቴጂያዊ ሚና በብቃት መወጣቷን እንደምትቀጥልበት ገልጸው፤ ከናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትም ጋር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ ግንኙነትን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በአፍሪካ በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ፣ የንግድ፣ የቱሪዝምና የትራንስፖርት ትስስርን ለማሳደግ እንደሚሰራም መግለፃቸውን ኢዚአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቷ ከሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችላትም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review