AMN ህዳር 20/2017 ዓ .ም
ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የሴክተሮች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ከፍተኛ ልዑ ከአዘርባጃን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስትር ሚካይል ጃባሮቭ ጋር በባኩ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በአረንጓዴ የኃይል አማራጭን ጨምሮ በተለያዩ ቁልፍ መስኮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናክርን ያለመ ነው።
የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትስስሩን ይበልጥ የሚያጠናክር የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት እንደሚገባም ተነስቷል።
በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያና አዘርባጃን የሁለትዮሽና የባለብዝሃ ወገን ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የአዘርባጃን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የንግድ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉም በውይይቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋም መስማማታቸውን በአንካራ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።