ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በተራዘመው የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ላይ ተስማሙ

  • Post category:ዓለም

AMN ህዳር 18/2017 ዓ .ም

ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በተራዘመው የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ላይ ተስማሙ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ባወጣው መረጃ የተራዘመ የብድር አቅርቦቱ ለአራት ዓመት የሚቆየው የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ማዕቀፍ ነው።

በአልቫሮ ፒሪስ የተመራ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ከሕዳር 3 እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጓል።

ቡድኑ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፕሮግራም እያደረገ ያለው ድጋፍ አፈጻጸምና የኢትዮጵያ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።

የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

ባለሙያዎቹ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባንኮችና የንግድ ተቋማት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በገበያ ወደ ሚወሰን የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ያደረገችው ሽግግርን ጨምሮ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ በመደበኛ እና የትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 በመቶ በታች እንዳወረደው ነው የቡድኑ መሪ የገለጹት።

የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ በባለሙያዎች ደረጃ የተደረሰውን ስምምነት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚገመግም ገልጸዋል።

ቀጣይ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ግምገማዎች በየስድስት ወሩ እንደሚካሄዱ ፒሪስ መግለጻቸውን የአይ ኤም ኤፍ አመልክቷል።

መርሃ ግብሩ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም መጽደቁ የሚታወስ ሲሆን የአይ ኤም ኤፍ ግምገማ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚለቀቅ ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review