AMN- ጥር 20/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ ፈርመውታል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በሁለቱ ሀገራት የተደረገው ስምምነት በትምህርቱ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።
በትምህርት ዘርፉ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸው የሚደረገው ድጋፍ ፍትሃዊና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለውን ሥራ እና በትምህርቱ ዘርፍ ትብብር የሚሹ ጉዳዮችን ለሚኒስትሯ አብራርተውላቸዋል።
ሚኒስትር አና ማሪያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጣሊያን አጋር መሆኗን አንስተው ሁለቱ ሀገራት በትምህርቱ ዘርፍ በላቀ ትብብር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
የተፈረመው መግባቢያ ስምምነት በጣሊያን እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ቀጥተኛ ትብብር እንዲኖር የሚያበረታታ ነው መባሉን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።