
AMN – ህዳር 3/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለቸውን የኢኮኖሚ ልማት ኢንሼቲቮች ለማሳካት የደን ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ ደን ልማት አዘጋጅነት በደን ልማት ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ(ፕ/ር) እንደገለፁት ደን የአፈር ለምነትን ከማሳደግ ባለፈ የውሃና የአካባቢ ስነ-ምህዳር ሚዛን ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።
በተጨማሪም የደን ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ዘላቂ የመሬት አጠቃቀምን ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት፣ ለውበትና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።
የደን ልማት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ ልማት ኢንሼቲቮች ለማሳካት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምር ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
የደን ልማት ስራው በጥናትና ምርምር ከተደገፈ አካባቢያዊ ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ ከውጭ የሚገቡ የደን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰሩ ስራዎች የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
በተሰራው ስራም የግብርና ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ የደረቁ ወንዞችና ዥረቶች ውሃ መያዝ መጀመራቸውን አውስተዋል።
የችግኝ ተከላው የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙና የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ ማስቻሉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።