ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት ትሰራለች – አቶ አደም ፋራህ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት ትሰራለች – አቶ አደም ፋራህ

AMN ግንቦት 23/2017

ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ የህንድ ፓርላማ ልዑክን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የህንድ የፓርላማ አባል በሆኑት ሱፕሪያ ሱሌ ከተመራው ልዑክ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል።

ህንድና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

ሀገራቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በሰላም ዙሪያ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።

የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችም ቀጣይነት ባለው መልኩ ገቢራዊ እንደሚደረጉ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በየዘርፉ ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር የመፍጠር ስራዎችን በትኩረት እያከናወነች እንደምትገኝም አንስተዋል።

የህንድ ልዑካን ቡድን መሪ ሱፕሪያ ሱሌ በበኩላቸው ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት ትሰራለች ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review