ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ትብብር የማሳደግ ፍላጎት አላት- ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ትብብር የማሳደግ ፍላጎት አላት- ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 23/2017

ኢትዮጵያ ከተባበበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሻ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የዲጂታልና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ልዩ ልዑክ አማንዲፕ ሲንግ ጊል (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ሽግግር እንዲሁም በሌሎች መስኮች ላይ ያላትን ዓለም አቀፍ ትብብርን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም ኢኖንፎርሜሽ እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በፈጠራቸው ማዕቀፎች ያላትን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንደምትሰራ አመልክተዋል።

ከተመድ የቴክኖሎጂ የስራ ክፍሎች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በአስተዳደርና በሰው አቅም ግንባታ ላይ በማተኮር የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያጎለብቱ ጠንካራ ፖሊሲዎች እና ተቋማት ማቋቋሟን በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የዲጂታልና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ልዩ ልዑክ አማንዲፕ ሲንግ ጊል (ዶ/ር) የደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ሃገራት በዲጂታል ዓለም እኩል ተጠቃሚ እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የተመድን የዲጂታል ዘርፍ እድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review