የኢትዮጵያ ከተሞች በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመናዊ የከተሜነት እሳቤ ዕድገትን ማሳለጥ እንደሚኖርባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው “ኑ ጎንደርን እንሞሽር” የጎንደር ከተማ ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቃል በመግባት ተጠናቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጦፋ ሙሐመድ፣ የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜም ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ የተገኘሁት በልማት ተግባር የተጉና የበረቱትን ኢትዮጵያዊያንን ለማመስገን ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ትልቅ ሃሳብ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ከተሞች የዕድገት መሰረቶች በመሆናቸው ሃብትን፣ ሃሳብን፣ ዕድገትን እና ዘመንን ማስተሳሰር እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኃያልነት ታሪኳ ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንት ታየ፤ መሠረቱ ከሕዝቦቿ ሀገር ወዳድነት ጋር የተሰናሰለ እሳቤ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር አብያተ መንግስታትን የመፍረስ አደጋ ለመታደግ ለወሰዱት ወሳኝ እርምጃ ምስጋና አቅርበዋል።
ለጎንደር ከተማ ልማት የገቢ መርሃ ግብር አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ያመሰገኑት ፕሬዝዳንቱ፤ ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰውና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ፈጥኖ ወደ እድገት ማማ ማስፈንጠር እንደሚቻል አንስተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የከተሜነት ታሪክ ከክትመት እስከ ኪነ ጥበብ፣ ከሥልጡንነት እስከ የታሪክ አሻራ ድረስ ጎንደር ለብዙ ከተሞች ምሳሌ ናት ብለዋል።
ይሁን እንጂ ልማት ተነፍጓት ባለችበት የመቆም እጣፋንታ ገጥሟት እንደነበር አስታውሰው፤ ቅርሶቿም ተጎሳቁለውና የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸው የቆየች ከተማ እንደነበረች ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተከናወኑ የጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች ዕድሳትና የልማት ስራዎች በከተማዋ ነዋሪዎች ደስታና አድናቆት እንደፈጠሩ ገልጸዋል።
አባቶቻችን ውብ አድርገው የሰጡንን ከተማ የመገንባት ኃላፊነት ወስደናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም ቅርስን ከማደስ ባለፈ የዕድገት ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር ከተማ ለዘመናት ከስልጣኔ ጋር የተሳሰረ ታሪክ ቢኖራትም ከዘመኑ ጋር የሚሄድ መሠረተ ልማት የላትም ብለዋል።
አሁን ግን ይህ እንዲያበቃም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለከፈቱት የብርሃን መንገድ ምስጋና አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ የፌዴራል መንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የክልል መንግስታት፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ባለሃብቶች የገንዘብ ድጋፍ ቃል የገቡ ሲሆን መርሃ-ግብሩም እስከ ግንቦት 30/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀጥል መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።