AMN- መስከረም 10/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰራች መሆኗን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) አስታወቁ
ከመስከረም 6 አንስቶ በኦስትሪያ ቪዬና ሲካሄድ የቆየው 68ኛው ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በአቶሚክ ኢነርጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ልማትን በማጎልበት በጤና፣ ግብርና፣ማኑፋክቸሪንግ፣ኃይል ልማትና በተለያዩ ዘርፎች ለመጠቀም የሚያስችሉ ጥረቶቿን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጉልህ ጥረት ያነሱት ሚኒስትሩ ኤጀንሲው ይፋ ባደረጋቸው ኢኒሼቲቮች ሀገሪቷን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር የሕክምና ማዕከላቶችን አቅም ለማሳደግና ተጨማሪ ማዕከላትን ለማስፋፋት እያከናወነች ያለውን ስራና የኑክሌር ኢንጂነሪንግ ፕሮግራም የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችን በልዩ ሁኔታ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
የጸጸ ዝንብ ማጥፊያ ፕሮጀክት ማዕከልን ለማጠናከርና በጉባኤው ይፋ በተደረገው ’Atoms4Food’ በተሰኘው መርሃ ግብር አማካኝነት ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።