ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ወዳጅነትና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሊል ከድር ገለጹ።
አምባሳደር ደሊል ከድር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አቅርበዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነትና በፓን-አፍሪካኒዝም መርህ ላይ የተመሰረተውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ የወዳጅነትና ወንድማማችነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማድነቅ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሂደትን በማስተናገድና በማሰናዳት ላደረገችው ጉልህ አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደር ደሊል በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን እና የደቡብ አፍሪካን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በባህል እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የትብብር ዘርፎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።