ኢትዮጵያ ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ ናት፦ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ ናት፦ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

AMN – ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ሰላምን እና ዕድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

አምባሳደር ታዬ ከትላንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሩሲያ ፌዴሬሽን ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ውስጥ በሚካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ሚኒስትሩ በብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ለብሪክስ አባልነቷ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ በአፅንኦት ገልጸው፣ ሀገሪቱ በብሪክስ ውስጥ ያላትን የጎላ ሚና ለማሳደግም ከብሔራዊ የልማት ትኩረቶቿ አኳያ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችን አብራርተዋል።

ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ልማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል ያደረጉ እና የጋራ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች በስበሰባው አፅንኦት የተሰጣቸው መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ለማስጠበቅም የባለብዙ ወገን ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ የልማት ፋይናንስ እና የዕዳ ስረዛ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሰላምን እና ዕድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review