የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ በመሆን Ethiopian Tech Expo (ETEX 2025) የተባለ ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ሊያዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመሆን በዛሬዉ እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ኤክስፖው ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የቴክኖሎጂ የስሕበት ማዕከል መሆን የሚያስችላትን እምቅ አቅም ለማሳየት እንደሚያስችላት ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ያስመዘገበችውን ስኬት ለማሳየት የሚያስችል መድረክ ነው ብለዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የሁነቱን ዓላማ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታርታፖች በዚህ ዓለማቀፍ መድረክ ላይ ስራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም በሳይበር ደህንነት ረገድ ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር የተሰሩ ስራዎች በመድረኩ ይዳሰሳሉ፡፡
በኤክስፖዉ ላይ ከ10ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የፖናል ውይይቶች እና የቴክኖሎጂ ውድድሮች ይኖራሉ።
በሳይበር ደህንነት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ ስማርት ከተማ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ትምህርት ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው ኤክስፖው ከግንቦት 8 እስከ 10 ፣ 2017 ዓ.ም በአዲስ ዓለማቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድየኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡