ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንቨስተሮች መድረክን አስተናገደች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንቨስተሮች መድረክን አስተናገደች

AMN-መስከረም 22/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዩሮቦንድ ባለቤቶችን ያሳተፈ ዓለም አቀፍ የኢንቨስተሮች ጥሪ መድረክን ያስተናገደች ሲሆን በስራ ላይ የዋለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያም በተመለከተ ገለጻ አድርጋለች፡፡

ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ቀጣይ ሂደቱን በተመለከተ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትንና ኢንቨስተሮችን ያሳተፈ ስኬታማ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ጥሪ የውይይት መድረክ ማካሄዷን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራው የበይነ መረብ ስብሰባ ሀገሪቱ ያለችበትን የኢኮኖሚ ቁመና፣ ብድርን በተመለከተ ስላደረገችው የመልሶ ማዋቀር ስልትና ዘላቂነት ዙሪያ የተሟላ ማብራሪያ መቅረቡም ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ዙሪያ ስላከናወነችው እና ተግባር ላይ ያዋለችው የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፍ ማሻሻያ ስላመጣው ግልፅ ውጤትም ዶክተር ኢዮብ ገልጸዋል፡፡

በአራት ምሰሶዎች ላይ የተገነባው ማሻሻያው፤ በዘላቂ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት እና ንግድ ከባቢን በመፍጠር፣ በየዘርፉ የምርት እድገት እንዲጨምር እና የሲቪል ሰርቪስ አቅምን በማሻሻል፤ ኢትዮጵያን በ2030 በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ዓላማ ያሳካል ብለዋል፡፡

ጥሪው በቡድን 20 የጋራ አሰራር መሰረትም የኢትዮጵያን አሁናዊ የብድር መልሶ ማዋቀር አቅም በትኩረት ማጤኑም ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ እና ግሽበትንና የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ዳግም ማጤንን ዓላማ ያደረገውን የፊስካል ፖሊሲ ትግበራን ጨምሮ የረጅም ጊዜ ዘላቂ ብድር አሰራርን እንደምታረጋግጥ አስምራበታለች፡፡

የኢትዮጵያ አሁናዊ ብድር የማግኘት አቅምና ፈተናዎች የውይይቱ መሰረታዊ ነጥቦች እንደነበሩም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አንስቷል፡፡

መንግስት ከባለስልጣናትም ሆነ ከንግድ አበዳሪዎች ጋር ድርድር በማድረግ የዕዳውን ዘላቂነት ለመመለስ እና ችግሮችን ለመፍታት በድጋሚ ቃል መገባቱንም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review