AMN – የካቲት 29/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ዘመናዊ ድሮኖችን ማምረት መጀመሯን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመረቱ ያየናቸው ድሮኖች ከጥቂት አመታት በፊት ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላትም ጭምር የሚጠበቁ አልነበሩም ሲሉ ገልጸዋል።
ከጥቂት አመታት በፊት ከጦር መኮንኖች ጋር የውጊያ መልኮች እየተቀየሩ በመሆናቸው፣ ወደ 4ኛው ጄኔሬሽን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በኤ አይ በኩል በስማርት ሴንሰርስ ለሚደረግ ጦርነት መዘጋጀት አለብን የሚል ውይይት አድርገን ነበር ብለዋል፡፡
ብዙ ሳንቆይ ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ችግር ሲገጥመን እነዚያን ያስቀመጥናቸውን የጦር አቅም አባዥ መሳሪያዎች፣ በተለይም ድሮን ለመግዛት በምንፈልገው አይነትና ቅርጽ አለማግኘት እንዲሁም በሻጮች እና በሌሎችም በኩል ጫና ይደርስብን ነበር ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ድሮን ከገዛንም በኋላ አጠቃቀሙ ላይ በፈለግነው ልክ “ኦፕሬት” ለማድረግ እንቸገር ነበር፣ ዛሬ ግን በጣም ዘመናዊና ስማርት ሴንሰር ያላቸው እና በኤ አይ የታገዙ በቀላሉ ማጥቃት የሚችሉ ሁለት ሳይድ ድሮኖችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርተው ማየት እንደ እኛ አይነት ህልመኛ ግለሰቦች በጣም አስደሳች ነው ብለዋል፡፡

በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለ ድሮን ጽንስ ሀሳብ ከመገንዘብ ባለፈ በሀገር ልጆች ማምረት መቻላችን በእጅጉ የሚያኮራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡
ዛሬ ያየነው አቅም ያለንን ሀይል የሚያባዛ፣ በኮሙኒኬሽን ደረጃ የምንጠቀምባቸውን ድሮኖቸ በስፋት ማምረት የሚያስችል አቅም ስለሆነ ማንኛውንም የሚገጥመንን ፈተና በመረጃ በመጠቀም የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በማወቅ እና በማክሸፍ ረገድ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል፣ ለፖሊስ ሰራዊት፣ ለደህንነት ተቋማት የሚሰጠው የማባዛት አቅም በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ይህን አቅም የበለጠ ለማሳደግና አዘምኖ ለመጠቀም ምርምር ማድረግና የገበያ ማፈላለግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ በሀገር ቤት የተመረቱት ድሮኖች ገዝተን ከምናስገባቸው ድሮኖች በብዙ መስፈርቶች የተለዩና የላቁ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማምረቱ ሂደት የሚመለከታቸው ተቋማት ትብብር አስፈላጊ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም በርብርብ መስራት ይጠበቅብናል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡
በአስማረ መኮንን