ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተሻገረ ፋይዳ ያለው ነው፡- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተሻገረ ፋይዳ ያለው ነው፡- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆንዋ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተሻገረ ፋይዳ ያለው መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በ16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የነበራትን ተሳትፎና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ከመታደባቸው ባለፈ ከተለያዩ የአባል ሀገራት መሪዎች ጋር የጎንዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን የግነኙነት መድረኮች ማሄዳቸውን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው፣ የአባል ሀገራቱ ፍላጎቶች፣ አቋሞች የተንፀባረቁበት፣ የተበታተኑ ድምጾች ወደ አንድ የመጡበት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ሀገሮች ድምፅ የተሰማበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን የሚስተዋለው ኢ-ፍትሀዊ የፋይናንስ አቅርቦት እና ሌሎችም ችግሮች እንዲፈቱ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በጉባኤው የአባል ሀገራቱን አንድነትና በቀጣይ የዓለም መድረኮች ላይ የጋራ ተፅዕኖዎችን መፍጠር የሚችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት መድረክ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለኢትዮጵያም የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት እድሎችን እንደሚያሰፋ ነው የገለጹት፡፡

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር በመሆኗ ሲንፀባረቅ የነበረውን ያልተገባ ሀሳብ የሻረ እና ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆንዋ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ያውሱት ለገሰ ቱለ (ዶ/ር) በጉባኤው የተንፀባረቁ አቋሞችና የተወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች የሚያሳኩ ሆነው ነው የተገኙት ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የዓለም መድረኮች በተደጋጋሚ ያነሷቸው የነበሩ አቋሞች በዚህ ጉባኤ በስፋት የተንፀባረቁበት እንደነበር ያብራሩት ሚኒስትሩ፣በተለይም በፀጥታው ምክርቤት ያለው የኢ-ፍትሃዊ ውክልና ጉዳይ መስተካከል እንዳለበት እና አፍሪካም ሆነች ኢትዮጵያ ተሰሚነታቸው እንዲጎላ ውክልና ማግኘት እንዳለባቸው በአባል ሀገራቱ መሪዎች በኩልም አቋም የተያዘበት ነበር ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፋይናንስ ልማት አካታችነት በተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች የታሰረ በመሆኑ ለሁሉም ተደራሽ ከመሆን አንፃር ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲጠቀስ የነበረውን ሀሳብ፣በዚህ ጉባኤ ላይ የሁሉም የብሪክስ አባል ሀገራት አቋም ሆኖ ለመንፀባረቅ መቻሉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር የመገናኘት እድል እንደፈጠረላት ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣በዚህም በተለይም ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት እያደረገች ያለውን የሰጥቶ መቀበል መርህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየሀገራቱ መሪዎች ጋር በነበራቸው የሁለትዮሸ ውይይቶች ላይ የኢትዮጵያን አቋም ለመግለጽ መቻላቸውን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ የጎንዮሽ ውይይቶች ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገቻቸው ያሉ ጥረቶችን እና እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን የገለጸች ሲሆን በተለይም በስንዴ ምርት ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመረት እየተደረገ ያለው ተነሳሽነት ለአባል ሀገራቱ መሪዎች ለማስረዳት እድል ተፈጥሯል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አደጋ የደቀነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ልማትና እየተገኘ ያለውን ውጤትም ለአባል ሀገራቱ መሪዎች ለማስገንዘብ ጉባኤው እድል እንደፈጠረም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በ16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ የኢትዮጵያ አቋሞች ይበልጥ የተነፀባረቀበት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የአባል ሀገራቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት እና የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት እድል ያገኙበት ስኬታማ ጉባኤ እንደነበር ነው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው የገለጹት፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review