AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) ግቦችን የሚያሳኩ የተለያዩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች እየተገበረች እንደምትገኝ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የምግብ ዋስትና ስርዓትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄድ ጀምሯል።
በስብሰባው መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እና ሌሎች የህብረቱ አመራሮች፣ የዩጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢና ናባንጃ፣ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ግብርና ለአፍሪካ ከዘርፍነት ባለፈ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥነት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ኑሯቸውን የሚመሩበት እና ለዘላቂ ልማት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።
በዚህ ረገድም የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) ማዕቀፍ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማሳደግ እና ዘላቂነት ላለው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የህዝብ እድገት፣ የከተሜነት መስፋፋት እና አሁን ላይ የሚታዩ ዓለም አቀፍ ቀውሶች በግብርናው ዘርፍ ላይ የጋረጠውን ፈተና በውል መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የካዴፕ ግቦችን ለማሳካት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተለያዩ ብሔራዊ ኢኒሼቲቮች እየተገበረች መሆኑን አንስተዋል።
በብሔራዊ ስንዴ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርቷ ወደ 23 ሚሊዮን ቶን ማደጉንና ይህም ሀገሪቱን ለ50 ዓመታት ስታስገባ የቆየውን ስንዴ በራሷ አቅም እንድታመርት አስችሏታል ነው ያሉት።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውንና ይህም የደን ሽፋኑን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን ጠቁመዋል።
መርሃ ግብሩ የማይበገር ስነ-ምህዳር እና የአኗኗር ዘይቤ ከመፍጠር አንጻር ወሳኝ ሚና መጫወቱንም አመልክተዋል።
የሌማት ትሩፋት(Bounty of basket) የእንስሳት ምርታማነትን ማሻሻልና በተለይም የዶሮ፣ የወተት፣ የአሳ፣ የስጋና የማር ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን እና ይህም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ኢኒሼቲቮቹ ከምግብ ስርዓት ፍኖተ ካርታ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የማይበገር እና ዘላቂነት ያለው የግብርናና የምግብ ስርዓት ለመገንባት ለተያዘው ራዕይ ስኬታማነት ኢኖቬሽን፣ አካታችነትና ዘላቂነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የግብርና እና የምግብ ስርዓቶቻችን ለአደጋዎች እና ፈተናዎች የማይበገሩ ለማድረግ የአቅርቦት ስንሰለትን ማጠናከር፣ ብዝሃ የምርት ስርዓትን መፍጠር እና በማህበራዊ ሴፍቲኔት ላይ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የወደፊቱ የአፍሪካ የግብርና እድገት መሰረት ወጣቶች እና ሴቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማጎልበት፣ አቅም መገንባት እና ሌሎች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ትውልድ ተሻጋሪ የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም እና የበለጸገች አህጉር ለመፍጠር የጋራ ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚያሻ ሚኒስትሩ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡