ኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች ማህበራት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (FIATA) የ2027 ዓለም አቀፍ ጉባኤን ለማስተናገድ ተመረጠች

You are currently viewing ኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች ማህበራት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (FIATA) የ2027 ዓለም አቀፍ ጉባኤን ለማስተናገድ ተመረጠች

AMN – መስከረም 23/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች ማህበራት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (FIATA) የ2027 ዓለም አቀፍ ጉባኤን ለማስተናገድ ተመርጣለች።

ሀገሪቱ ይህን አለም አቀፍ ጉባኤ ለማካሄድ መመረጧ በአፍሪካ አህጉር በሎጂስቲክስ ዘርፍ እየጎለበተ የመጣውን ሚናዋን በጉልህ የሚያመላክት ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊና የመርከብ አገልግሎት ወኪሎች ማህበር ይህን ጉባኤ በሀገሪቱ እንዲያሰናዳ መታጨቱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላ አህጉሪቱ ትልቅ እመርታ መሆኑም ተነግሯል።

ይህ ውሳኔ ዓለም አቀፉ የዘርፉ ፌዴሬሽን ታሪካዊ እርምጃ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ነው የተባለው።

ጉባኤው በአስደናቂ ፍጥነት በለውጥ ግስጋሴ ላይ በምትገኘው ደማቋ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል።

የማህበሩ የአዲስ አበባ ፕሬዚዳንት ዳዊት ውብሸት የጉባኤውን መካሄድ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እንድናካሂድ መመረጣችን ለሀገራችን ብሎም እንደ አህጉር ለመላው አፍሪካ አስደሳችና የሚያኮራ ብስራት ነው ብለዋል።

ጉባኤው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ግዙፍ መድረክ መሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው ያስረዱት።

ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የሚደረገው በአስደናቂ እድገቷ የባህል ማዕከልነቷና በቀጠናውም ሆነ በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ ትልቅ ስፍራ በሚሰጣት ከተማችን አዲስ አበባ መሆኑ ታላቅ ክብር ነው ብለዋል።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ጉባኤው በአፍሪካ እንዲካሄድ መወሰኑ አህጉሪቱ በተለይም ኢትዮጵያ በንግዱና በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ ወሳኝነት አመላካች ነውም ብለዋል።

በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአቀማመጧ የቀጣናዊ ስትራቴጂያዊ ሀገር በመሆኗ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት ሀገራችን ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በማስተናገድ በዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ዝግጁ መሆኗንም አስምረውበታል።

ጉባኤው በንግዱና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የአህጉሪቱን ሚና በማስተጋባትና የወደፊቱን የአቅርቦት ሰንሰለት በማመላከት ረገድ ትልቅ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ከ800 በላይ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ የዘርፉ ታላላቅ አመራሮችና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉበት ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review