ኢትዮጵያ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማረጋገጥ ላይ ናት-ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማረጋገጥ ላይ ናት-ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማምጣት ላይ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት ረገድ የረጅም ጊዜ ባለ ታሪክ መሆኗንም ገልፀዋል።

የዛሬው የሥልጠና ርዕሰ ጉዳይ “የፀጥታና ደህንነት እመርታ” የሚል ሲሆን በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጽህፈት ቤቶች አመራሮች የሥልጠናው ገለፃ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀርቧል።

ም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ባቀረቡት ገለፃ ሀገራችን የፀጥታና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት ረጅም አመታትን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን እነዚህ ተቋማት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አልፈው እንደ ኮሪያ፣ ኮንጎ እና በሌሎች ሀገራት በመሰማራት ሰላም የማስከበር ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት የቻሉ ናቸው ብለዋል።

ተቋማቱ የየራሳቸው ጥንካሬ ቢኖራቸውም የነበረባቸው ክፍተት ሊያርም በሚችል መልኩ አሁን ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አነሳሽነት ወቅቱን በሚመጥን ደረጃ የሪፎርም ሥራ በመሠራቱ ከፍተኛ አቅም ለመፍጠር ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ዘመኑ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ የበላይነት ፉክክር የሚታይበት ብቻ ሳይሆን የጦርነትም በመሆኑ ኢትዮጵያም ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የራሷን የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን የመገንባትና በሪፎርም የማጠናከር ሥራ ሠርታለች፤ ትሰራለችም፤ ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም መከላከያን ጨምሮ በፀጥታ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት እና በፋይናንስ ደህንነት የተጠናከረ የሪፎርም ሥራ መሰራቱንም ነው ም/ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ያብራሩት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review