ኢትዮጵያ ግብጽ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ለቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢ ሚና እንድትወጣ አሳሰበች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ግብጽ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ለቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢ ሚና እንድትወጣ አሳሰበች

AMN- መስከረም 20/2017 ዓ.ም

ግብጽ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ በቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢ ሚና ልትወጣ እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ገለጹ።

ግብጽ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ወደ ሰላማዊ የትብብር አማራጭና ውይይት ዳግም እንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።

79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒውዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በተመድ የግብጽ ተወካይ በጠቅላላ ጉባዔው ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ላይ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ላቀረበችው የሐሰት ክስ ምላሽ ሰጥታለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የስነ ስርዓት ደንብ ላይ የተቀመጠውን ምላሽ የመስጠት መብት (First Right of Reply) ተጠቅመው ግብጽ ላነሳቸው ሀሳብ መልስ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ የግብጽ ተወካይ በኢትዮጵያ ላይ ተገቢነት የሌለው አስተያያት መስጠቷን በንባብ ባቀረቡት ምላሽ ላይ አንስተዋል።

ግብጽ በተወካዩ ንግግር ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ለመቀየር የምታደርጋቸውን ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ሀሳብ ማንሳቷ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ናይል የኢትዮጵያ እና ግብጽ የትብብርና ለሁለቱ እህትማማች አገራት ሕዝቦች የጋራ ሰላምና ብልጽግናን የሚፈጥር ዋንኛ የመተሳሰሪያ መንገዳቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ግብጽ ላይ ምንም አይነት ጉዳት የማድረስ ፍላጎት እንደሌላት የገለጹት አምባሳደሩ ይሁንና ግብጽ ሉዓላዊ አገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለዜጎች ጠቀሜታ የማዋል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ ተቃርና ቆማለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ የፋይናንስ አቅም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እየገነቡ እንደሚገኝና ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎታቸው ብርሃን እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ግድቡ ቀጣናውን በኢነርጂና የንግድ መስክ ትስስር እንደሚፈጥርም ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያን ሁለት ሶስተኛ ክፍል የሚነካና የአገሪቷ 70 በመቶ የውሃ ምንጭ ነው ያሉት አምባሳደር ዮሴፍ ይሁንና ኢትዮጵያ ይህን የውሃ ሀብት ይዛ የምግብ እና ኢነርጂ ዋስትናዋን በሚፈለገው መልኩ ማረጋገጥ አልቻለችም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልገው ጠቁመው ኢትዮጵያ ይህን ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት ማስቆም እንደማይቻል አስገንበዋል።

ዜጎቻችን ክብር ያለው ሕይወት አይገባቸውም ብሎ መናገር ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት መሆኑን በውል ትገነዘባለች ያሉት አምባሳደሩ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት የውሃ ሀብቱን በፍትሐዊነትና እኩልነት መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የተፋሰሱ አገራት በተስማሙባቸው የናይል ቤዚን ማዕቀፎች መስተናገዳቸው ትብብሩን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።

የአባይ ወንዝ 85 በመቶ ፍሰቱ ከኢትዮጵያ መሆኑን ገልጸው ሌሎቹ የተፋሰስ አገራት ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መልኩ በትብብር መልማትን አማራጫቸው ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁንና ለውሃ ሀብቱ ምንም ድርሻ የሌላት ግብጽ ዓለም አቀፍ መርሆዎችና የትብብብር ማዕቀፎችን ዋጋ ለማሳጣት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን የትብብር ማዕቀፎችን መሰረት አድርጋ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ኢ-ሚዛናዊ እሳቤ በውሃ ሀብት የመልማት ጥረቶች እውን እንዳይሆኑ እክል እየፈጠረች መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ሀብቷን ፍትሐዊነትና እኩልነት በሰፈነበት መልኩ መጠቀሟን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ግብጽ ጊዜ ያለፈባቸውን የቆዩ ማዕቀፎች ተጠቅማ የናይል ወንዝን ፍሰት እኔ ብቻ ልቆጣጠር የሚለውን ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ ትታ ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራርና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ የድርድር አማራጭን እንድትከትል ጥሪ አቅርበዋል።

ግብጽ በቅርቡ ወደ ትግበራ የሚገባው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በማጽደቅ በቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢና እንድትወጣ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተፋሰሱ አገራት ጋር ወደ ሰላማዊ የትብብር አማራጭና ውይይት ዳግም እንድትመልስም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review