ኢትዮጵያ 3 የእጅ ኳስ ክለቦቿን በአፍሪካ ክለቦች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ታሳትፋለች

You are currently viewing ኢትዮጵያ 3 የእጅ ኳስ ክለቦቿን በአፍሪካ ክለቦች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ታሳትፋለች

AMN – መስከረም 29/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ 3 የእጅ ኳስ ክለቦች በሞሮኮ ላዩን ከተማ በሚካሄደው የ45ኛው የአፍሪካ ክለቦች የወንዶች እና ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።

በውድድሩ መቻል እጅ ኳስ ክለብ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ክለብ እና መቀሌ 70 እንደርታ እጅ ኳስ ክለብ ከኢትዮጵያ ይሳተፋሉ፡፡

3 ክለብ ማሳተፍ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ያሉት የኢትዮጵያ እና የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍትህ ወልደሰንበት፣ በውድድሩ ከመላው አፍሪካ 16 የወንድ እና 12 የሴት ክለቦች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

ውድድሩ እ.ኤ.አ ከነገ ጥቅምት 10 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 19 2024 በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ላዩን ከተማ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

በወጣው ምድብ መቻል እጅ ኳስ ክለብ ከቤኒኑ አድጂድጃ፣ ከሞሮኮው ዋይዳድ እንዲሁም ከሴኔጋሉ አስፋ ጋር ተደልድሏል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ክለብ ከግብፁ ዛማሊክ፣ ከሞሮኮው ማውንታዳ እንዲሁም ከካሜሮኑ ፍሬንድሺፕ ክለቦች ጋር የተደለደለ ሲሆን መቀሌ 70 እንደርታም ከግብፁ አልሀሊ፣ ከኮንጎው ኢትኦይሌ እንዲሁም ከኮንጎው ሲኤፍጄኤሶ ጋር መደልደላቸውን የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ባወጣው የውድድር መርሐግብር ተመላክቷል፡፡

በወጣው ድልድል መሠረትም ቂርቆስ በመክፈቻው እለት የግብፁን ዛማሊክን ሲገጥም መቻል የቤኒኑን አድጂድጃ እንዲሁም መቀሌ 70 እንደርታ በሁለተኛው ቀን የግብፁ አልሀሊን በመግጠም የመጀመሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ከፌዴሬሽኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review