AMN-የካቲት 5/2017 ዓ.ም
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የኩባንያውን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለመገናኛ ብዙኃን አቅርበዋል።
ኩባንያው በዓለም ካሉ 781 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 17ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በአፍሪካ ካሉ 198 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 1ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የኩባንያው የደንበኞች ቁጥር 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማፍራቱን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይህ አሐዝ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ከነበረው የደንበኞች ቁጥር የ7.9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 61 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ኩባንያው በውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያገኝባቸው ምንጮች 72 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮ-ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት አጋማሽ 61.9 ቢሊዮን ብር አትርፏል።
ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ከ43% በላይ እድገት መመዝገቡ ተመላክቷል።
ኩባንያው በተገበረው የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂ 3.5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ይህም የዕቅዱን 134 በመቶ ማሳካት የተቻለበት መሆኑን አመላክተዋል።
በተያያዘ ቴሌብር 51 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን እስካሁን 1 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈፀሙን ስራ አስፈፃሚዋ አመላክተዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም 4.2 ሚሊየን የናሽናል አይዲ ፋይዳ መታወቂያ የተመዘገቡ ሲሆን ለ256 ሺ ዜጎች ታትሞ መሠጠቱን ተመላክቷል።
በመሀመድኑር አሊ