ኢትዮ ቴሌኮም ከ74 በመቶ በላይ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ

You are currently viewing ኢትዮ ቴሌኮም ከ74 በመቶ በላይ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ

AMN- መስከረም 9/2017 ዓ.ም

የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዱን ይፋ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም ለዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፋያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት መያዙንም አስታውቋል።

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሊድ ግሮውዝ የተሰኘ የ3 ዓመታት የዕድገት ስትራቴጂ ተግባራዊ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዓመትም ለስትራቴጂው ስኬት የተለያዩ ዕቅዶችን መያዙን አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ 5 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞች ለማፍራት ያቀደው ኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱንም አስታውቋል። ይህም ድርጅት ባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ካገኘው 93 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የ74 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ አለው።

በ2017 ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ጋር በተገናኘም በስትራቴጂው ላይ ማሻሻያዎችን ማድረጉን የገለፁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበጀት ዓመቱ የቴሌኮም አገልግሎትን በሽፋንም በአቅምም ለማስፋፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በ2017 ከ1ሺህ በላይ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት ማቀዳቸውን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ከግንኙነት ባሻገር ያሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና መፍትሔዎችን ማቅረብ ላይ በበጀት ዓመቱ ሰፊ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያለው ድርጅቱ

በዚህ ዓመት 500 ከተሞችን የ4ጂ፣ 15 ከተሞችን ደግሞ የ5ጂ ኔትዎርክ ሽፋን እንዲኖራቸው ማቀዱንም አስታውቋል።

ይህም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ አቅም ይሆናል ተብሏል።

እንደ ክላውድ ያሉ የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራ እንደሚሰራ የገለፀው ድርጅቱ ለዲጂታለ መሰረተ ልማት ማስፋፋያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት መያዙንም ገልጿል።

በአሰግድ ኪዳነ ማርያም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review