ኢንስቲትዩቱ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን የሚመዘግብና የሚያጋራ ዲጂታል የመረጃ ቋት(portal) በይፋ ስራ አስጀመረ

You are currently viewing ኢንስቲትዩቱ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን የሚመዘግብና የሚያጋራ ዲጂታል የመረጃ ቋት(portal) በይፋ ስራ አስጀመረ

AMN – የካቲት 3/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት የመሬትና መሬት ነክ መረጃዎችን የሚመዘግብና የሚያጋራ ዲጅታል የመረጃ ቋት(Portal) በይፋ ስራ አስጀመረ፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የጂኦስፓሻል ዳታ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ሀገራዊ የመሬት መረጃ አስተዳደርና ስርጭትን የሚያሳልጥ(ESRI Enterprise Portal) ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ስራ አስገብቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ስትራቴጂ ቀርጻ እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።

ይህ ስትራቴጂ የሀገሪቱ የልማት እቅድ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ማህበረሰብ ማፍራት ለሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው ዲጂታል የጂኦስፓሻል ፖርታል በኢትዮጵያ የመሬት መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የማስተዳደር፣ የማጋራትና የመጠቀም አቅምን በእጅጉ የሚያሻሽል ነው ብለዋል።

የጂኦስፓሻል መረጃዎች ለውሳኔ ሰጪዎች ወሳኝ እንደሆኑ ጠቅሰው፥ በተለይም በከተማ ፕላን፣ በግብርና፣ በአደጋ ስጋት አመራር እና በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላቸው ፀሐይ እንደገለጹት፤ ዲጂታል መሰረተ ልማቱ የጂኦስፓሻል ዳታ መሰረተ ልማት ዝርጋታን እውን በማድረግ ሀገራዊ የመረጃ አስተዳደርና ስርጭትን የሚያሳልጥ ነው።

ዲጂታል መሰረተ ልማቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን የተናበበ የመረጃ አጠቃቀም እንደሚያጎለብትም አመላክተዋል፡፡

የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት(ጂአይዜድ) የጂኦስፓሻል ፕሮጀክት አማካሪ ቱሉ በሻህ(ዶ/ር)፤ የመሰረተ ልማቱ ይፋ መሆን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን መናገራቸውን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review